መከላከያ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ተቃርቧል

አንጋፋው መከላከያ ዛሬ ማሸነፉን ተከትሎ ወደ 2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ በእጅጉ ተቃርቧል።

ሀዋሳ ላይ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሊጠናቀቅ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ይቀራሉ። ዛሬ ረፋድ መከላከያ በደረጃው ሦስተኛ ላይ የሚገኘውን ገላን ከተማን 4ለ0 በማሸነፍ ነጥቡን 32 አድርሶ ከተከታዩ ኤሌክትሪክ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ማስፋት ችሏል።

የዮሐንስ ሳህሌውን ቡድን የማሸነፍያ ጎሎች የገላኑ ተከላካይ ያሬድ ታረቀኝ በራሱ ላይ፣ ጋናዊው አጥቂ ኤርነስት ባራፎ እና ዘካሪያስ ፍቅሬ ከእረፍት በፊት እንዲሁም ከእረፍት መልስ ቴዎድሮስ ታፈሰ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሆነዋል።

መከላከያ በቀጣዩ ጨዋታ ከሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ካሳካ ወይም ኤሌክትሪክ በደሴ ነጥብ ከጣለ በቀጥታ ወደ 2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማለፉን ይረጋገጣል፡፡

ጦሩ በፕሪምየር ሊጉ ከ1997 ጀምሮ ሲወዳደር ቆይቶ በ2011 ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ