ሪፖርት | አራት ግቦች የተስተናገዱበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል

የሀያኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ የሆነው የሰበታ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ጅማ አባጅፋርን አሸንፈው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት የሰበታ ከተማው አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ሦስት ነጥብ ካገኙበት ቋሚ አሰላለፍ አምስት ለውጦችን በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ክሪዚስቶም ንታምቢ፣ ቃልኪዳን ዘላለም፣ ያሬድ ሀሰን እና አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ በማሳረፍ በመሳይ ጳውሎስ፣ አብዱልባሲጥ ከማል፣ ናትናኤል ጋንቹላ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ እና ፉዐድ ኢብራሂምን ተክተው አስገብተዋል። ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ከፍተኛ ችግር የነበረበት ወላይታ ድቻ በበኩሉ ምንም እንኳን ዋና አሠልጣኙ ዘላለም ሽፈራውን በበሽታው ምክንያት ሜዳ ላይ ባያገኝም በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በቋሚነት የማሰለፉ ዕድል አግኝቶ ለጨዋታው ቀርቧል። በሀዋሳው ጨዋታ አጥቂ ሆኖ የተጫወተው መክብብ ደገፉ ዛሬ ወደ መደበኛ ቦታው (ግብ ጠባቂነት) ሲመለስ በውድድር አጋማሽ በነበረ የዝውውር መስኮት ቡድኑን የተቀላቀለው ኢዙ አዙካም የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ሜዳ ገብቷል።

ጨዋታው ገና በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ የቅጣት ምት ያገኙት ወላይታ ድቻዎች አጋጣሚውም በአጥቂያቸው ስንታየሁ መንግስቱ አማካኝነት ለመጠቀም ጥረው የግብ ዘቡ ምንተስኖት አሎ ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶባቸዋል። ወደ ውጪ የወጣውን ኳስ ድቻዎች በመዓዘን ምትነት አሻግረውት የነበረውን ቢሆንም ምንተስኖት በድጋሜ በመቆጣጠር ለአጥቂዎቹ የላከው ኳስ ቡድኑ መሪ የሆነበትን ጎል እንዲያገኝ አድርጓል። በዚህም በ5ኛው ደቂቃ ምንተስኖት በረጅሙ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በእጁ የላከውን ኳስ በሚገባ ማፅዳት ያልቻለው አናጋው ባደግ ኳሱን ቡልቻ ቀምቶት ሰበታዎች የድቻ ግብ ክልል ደርሰዋል። ቡልቻም በጥሩ ሁኔታ ኳሱን ለኦሴ ማውሊ አመቻችቶለት ማውሊ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ቡልቻ በድጋሜ በተመሳሳይ በግራ መስመር ያገኘውን ኳስ በመጠቀም የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ለማሳደግ ቢጥርም መክብብ ውጥኑን አክሽፎበታል።

አጀማመራቸው እጅግ መልካም ሆኖ የታየው ሰበታ ከተማዎች በ18ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም ማውሊ ከቅጣት ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ወደ ግብ ሲመታ ግብ ጠባቂው መክብብ ፊት ለፊት ኳሱን በመትፋቱ አለማየሁ ሙለታ አግኝቶት የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። በተቃራኒው ገና ጨዋታው 20 ደቂቃ ሳይሞላው ከባድ ፈተና ያጋጠማቸው ድቻዎች የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በመፍጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲቸገሩ ታይቷል። በተለይም ቡድኑ የሰበታ ከተማን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወደ ራሱ ለማምጣት ተቸግሮ ታይቷል። ጨዋታው ግማሽ ሰዓት ካስቆጠረ በኋላ ግን የአሠልጣኝ ዘላለም ተጫዋቾች በተሻለ ለመጫወት ጥረዋል። በ33ኛው ደቂቃም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ኢዙ ለስንታየሁ በግንባሩ አቀብሎት ቁመተ መለሎው አጥቂ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ይህንን ዕድል ያልተጠቀመበት ስንታየሁ በነፃ አቋቋም ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በ39ኛው ደቂቃም ኢዙ አዙካ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ስንታየሁ አንተነህ እና ኃይለሚካኤል መሐል ራሱን ነፃ በማድረግ ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎችም ድቻዎች ተሽለው ቢንቀሳቀሱም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። አጋማሹም በሰበታ ከተማ 2-1 መሪነት ተገባዶ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር ያሳየው የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ለማስተናገድ በርከት ያሉ ደቂቃዎች መጠበቅ የግድ ብሎታል። በአንፃሩ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች የነበራቸውን ተነሳሽነት አሁንም ያላጡት ድቻዎች አቻ የሚያደርጋቸውን ጎል ፍለጋ መታተር ይዘዋል። በዚህም በ68ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት በግራ እግሩ በመታው እና ተከላካዮች ተደርበው ወደ ውጪ ባወጡበት ኳስ የሰበታን የግብ ክልል ፈትሸዋል።

በተቃራኒው ያገኙትን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ታትረው መጫወት የቀጠሉት ሰበታዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የነበራቸውን ብልጫ በተወሰነ መልኩ ቀንሰው ታይተዋል። በተለይም ቡድኑ ለማጥቃት ያለው ፍላጎት ወርዶ ነበር። እርግጥ የቡድኑ አሠልጣኝ አብርሃም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው ቢያስገቡም በታሰበው መልኩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው ቀጥሏል።

አሁንም የሰበታ የግብ ክልል የደረሱት ድቻዎች በ80ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል። በዚህም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ቸርነት እግር መነሻን ያደረገ ኳስ በረከት እና ራሱ ቸርነት ጥቃት ቢፈፅሙም ተከላካዮች እና ምንተስኖት ዕድሎቹን አምክነውታል። ከሦስት ደቂቃ በኋላ ግን ድቻ የልፋቱን ውጤት አግኝቷል። በዚህም የሰበታ ተከላካዮች የራስ ምታት ሆኖ ያመሸው ቸርነት ከሳጥን ውጪ ስንታየሁ በግንባሩ ያመቻቸለትን ኳስ በመጠቀም ወደ ምንተስኖት የመታው ኳስ መረብ ላይ አርፎ ድቻ አቻ ሆኗል። ከሁለት ለባዶ መሪነት አቻ የሆኑት ሰበታዎች በ89ኛው ደቂቃ ፍፁም በሞከረው ኳስ ዳግም መሪ ለመሆን ሞክረው ነበር። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናደግ ጨዋታው 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ከሁለት ለምንም መሪነት ነጥብ የጣሉት ሰበታዎች በ23 ነጥቦች ያሉበት ስምንተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ከመመራት ተነስተው ያገኙትን አንድ ነጥብ ከዚህ በፊት ከሰበሰቡት ነጥብ ላይ በማከል በአጠቃላይ በ25 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቅጠዋል።



© ሶከር ኢትዮጵያ