ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ23ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በመመርኮዝ ይህንን የምርጦች ቡድን ሰርተናል።

አሰላለፍ: 3-2-3-2

አቡበከር ኑሪ (ጅማ አባ ጅፋር)

ወጣቱ ግብ ጠባቂ ቡድኑ ከወላይታ ድቻ ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ጠንካራ ሙከራዎችን በማዳን ጥሩ ቀን አሳልፏል። በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ የድቻዎችን በርካታ ተሻጋሪ ኳሶች በጥሩ ሁኔታ ከመቆጣጠር በተጨማሪ ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን ማዳን የቻለ ሲሆን ከፊቱ ከነበሩት ተከላካዮች ጋር የነበረው መናበብ መልካም የሚባል ነበር።

መላኩ ወልዴ (ጅማ አባ ጅፋር)

ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የገባው ተከላካዩ የከትሮ አጣማሪዎቹ አሌክስ አሙዙ እና ኤልያስ አታሮ ባይኖሩም የኋላ ክፍሉን በማደራጀት እና ከከድር ኸይረዲን ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ቡድኑ አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስተዋፅኦ አድርጓል። ከእረፍት በፊት አንተነህ ጉግሳ የሰነዘረውን ጠንካራ ሙከራ በድንቅ ሁኔታ ተደርቦ ያወጣበት በጨዋታው የሚጠቀስ ድንቅ መከላከል ነበር።

አሚን ነስሩ (አዳማ ከተማ)

መውረዱን ያረጋገጠው አዳማ ከተማ ከ12 ጨዋታ በኋላ ወደ ድል እንዲመለስ ጥሩ አበርክቶ ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል የመሐል ተከላካዩ አሚን ነስሩ ይጠቀሳል። በመስመር ላይ ያተኮረው የሀዋሳን ጥቃት በመመከት ጥሩ ቀን ያሳለፈው አሚን የግራ ተከላካዩ ሚልዮን ሰለሞን ለማጥቃት ወደፊት ሲጓዝ የሚተወውን ክፍት ቦታ በመሸፈን እና አንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ የበላይነት በመውሰድ ረገድ ጥሩ ቀን አሳልፏል።

ሰንዴይ ሙቱኩ (ሲዳማ ቡና)

ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን በረታበት ጨዋታ በጨዋታ ሳምንቱ መረቡን ሳያስደፍር የወጣ ብቸኛው ቡድንም ሆኗል። ለዚህ ስኬትም በመሀል ተከላካይነት የተሰለፈው ኬናዊው ሰንዴይ ሚና ትልቅ ነበር። የጨዋታውን ወሳኝነት በሚመጥን የትኩረት ደረጃ ላይ ሆኖ የተመለከትነው ተጫዋቹ ሳላዲን ሰዒድን በመቆጣጠር ከስህተት በራቁ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች አሸንፎ በመውጣት የተጋጣሚውን የማጥቃት ኃይል ሲያከስም ታይቷል።

ብርሀኑ አሻሞ (ሲዳማ ቡና)

ብርቱው የተከላካይ አማካይ በድጋሚ በሊጉ ካሉ የቦታው ምርጦች ውስጥ አንዱ መሆኑን ያሳየበትን የጨዋታ ሳምንት አሳልፏል። በመጨረሻ ጨዋታው መልክ የያዘ የመሰለውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የአማካይ ክፍል የግብ ዕድል የመፍጠር አቅም ተዳክሞ እንዲውል የብርሀኑ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ይታዩ የነበሩ አልፎ አልፎ ኃይልንም የቀላቀሉ ውሳኔዎች ለተከላካይ ክፍሉ ተፈላጊውን ሽፋን እንዲሰጥ አስችለውታል።

ሚካኤል ጆርጅ (ሀዲያ ሆሳዕና)

የሚካኤልን የዚህ ሳምንት ብቃት ያየ ሰው የጨዋታ ፍላጎት ከመጫወቻ ቦታ በላይ ለሜዳ ላይ ስኬት ያለውን ሚና በሚገባ ይረዳል። ከአጥቂነት ወደ አማካይነት ተለውጦ የተጫወተው ሚካኤል አንድ ግብ አስቆጥሮ ለሁለተኛው ግብ መነሻ የሆነ ከባድ ሙከራ ከማድረጉ በላይ በእንቅስቃሴ ሰፊ ሜዳ ሸፍኖ በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ሒደት ውስጥ ይገኝ የነበረበት ሁኔታ እና ከኳስ ጋር የነበረው ውሳኔ ልዩ ሆኖ ውሏል።

በቃሉ ገነነ (አዳማ ከተማ)

አዳማ ከተማ መውረዱን ካረጋገጠ በኋላ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ድል ሲቀናው በቃሉ ገነነ ያሳየው ብቃት ድንቅ ነበር። የአጥቂ አማካዩ በቃሉ ቡድኑን አሸናፊ ያደረጉ ሁለት የአብዲሳ ጀማል ጎሎች ሲቆጠሩ ኳሶቹን በማሻገር (ከቀመ ኳስ) ተሳትፎ አድርጓል። ከዚህ ውጪም ቡድኑ በመከላከል አደረጃጀት ቅርፁን ጠብቆ እንዲጫወት ወደ ኋላ እየተመለሰ ክፍተቶችን ለመዝጋት ያደረገው መታተር መልካም ነበር።

ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

የባህር ዳር ከተማው የአጥቂ አማካይ ፍፁም ዓለሙ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም በግሉ ምርጥ ጊዜን አሳልፏል። በተለይ አይደክሜው ተጫዋች የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ስህተት እንዲሰሩ ፍጥነት እና ቅልጥፍና የታከለባቸው እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ቡድኑን ለመጥቀም ሲጥር ነበር። ይህ ልፋቱም ፍሬያማ ሆኖ የቡድኑን የመጀመሪያ ጎል በዚሁ መንገድ አስቆጥሯል። ከጎሉ በተጨማሪም በመስመሮች መካከል እየገባ የቡናን የመከላከል አደረጃጀት ሲፈትን የነበረበት ሒደት መልካም ነበር።

ኦሴ ማዉሊ (ሰበታ ከተማ)

ሰበታ ከተማ በተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና በአሳማኝ ሁኔታ ቢበለጥም ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ያደረገው የኦሴ ማዉሊ መኖር ነበር። ተጫዋቹ ቡድኑ በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ሳጥን የደረሰባቸውን ቅፅበቶች ፍሪያማ አድርጓቸዋል። ሁለት ኳሶችን በአግባቡ ተቆጣጥሮ ፍፁም ቅጣት ምት ሲያሰጥ አንዱን ደግሞ ለዱሬሳ ወሳኝ ግብ አመቻችቷል። ሁለቱ ፍፁም ቅጣት ምቶችም በጋናዊው አማካይነት ጎል ሆነዋል። ማውሊ በፊት አጥቂነት ጨዋታውን ቢጀምርም ከዚህ ቀደም በመስመር ተጫዋችነት ሚና መጫወቱን ከግምት በማስገባት በመስመር አጥቂነት አካተነዋል።

ሪችሞንድ አዶንጎ (ድሬዳዋ ከተማ)

ዘንድሮ 767 ደቂቃዎችን ለድሬዳዋ ከተማ የተጫወተው ሪችሞንድ አዶንጎ በዚህ ሳምንት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል። ከምንም በላይ ተጫዋቹ መረብ ላይ ያሳረፋቸው ጎሎች ድሬዳዋ እጅግ ወሳኝ ድል እንዲያገኝ አስችሎታል። በተለይ ደግሞ አዶንጎ ጎሎቹን ሲያስቆጥር ያሳየው ቦታ አያያዝ እና የአጨራረስ ብቃት የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንድናካትተው አድርጎናል።

አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)

የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሪከርድ ለመስበር እየተንደረደረ የሚገኘው አቡበከር ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ሁለት ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል። በተለይ ተጫዋቹ የመጀመሪያውን ጎል የግብ ጠባቂውን አቋቋም ተመልክቶ ማስቆጠሩ እንዲሁም ሁለተኛውን ጎል ደግሞ በድንቅ ሁኔታ ከቅጣት ምት ማግኘቱ አሁንም ምርጥ ብቃቱ ላይ እንደሚገኝ ያመላከተ ነው። ከዚህ ውጪም አብዛኛውን የሁለተኛ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር የተጫወተውን ቡድኑን ወደ ኋላ እየመጣ ሲያግዝ የነበረበት መንገድም አድናቆት የሚያሰጠው ነበር።

አሰልጣኝ: ገብረመድኅን ኃይሌ (ሲዳማ ቡና)

ከባድ የነበረውን ሲዳማ ቡናን የማትረፍ ሂደት ከተደጋጋሚ ሽንፈቶች በኋላ በፈለጉት መንገድ እየመሩ ያሉት አሰልጣኝ ገብረመድኅን በሳምንቱ ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል። ከአሸናፊነት የተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሲዳማ ከባድ ተጋጣሚ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም የአሰልጣኙ የጨዋታ ዕቅድ ሰርቶ ሲዳማ ከብልጫ ጋር 2-0 በማሸነፍ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን አለምልሟል።

ተጠባባቂዎች

ፍሬው ጌታሁን (ድሬዳዋ ከተማ)
ደስታ ጊቻሞ (አዳማ ከተማ)
ዐወት ገብረሚካኤል (ድሬዳዋ ከተማ)
ያስር ሙገርዋ (ሲዳማ ቡና)
አብዱልከሪም ወርቁ (ወልቂጤ ከተማ)
አብዲሳ ጀማል (አዳማ ከተማ)
ዳዋ ሆቴሳ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ኦኪኪ አፎላቢ (ሲዳማ ቡና)