ወላይታ ድቻ መንቃት ጀምሯል

በበርካታ ደጋፊዎች በዚህ ሁለት ቀናት ተቃውሞን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ የሦስት ነባር ተጫዋቾችን ውል ለማራዘም ቅድመ ስምምነት ፈፀመ፡፡

አጀማመሩ የከፋ የነበረው ነገር ግን በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት ላይ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከቀጠረ በኋላ የተሻለ ውጤት ያመጣው ወላይታ ድቻ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት በጅማ አባጅፋር ያሳለፉትን አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በቅርቡ በአንድ ዓመት የውል ዕድሜ መቅጠር ቢችልሞ ወደ ዝውውር ገበያውም ሆነ የተጫዋቾችን ውል ከማራዘሙ ተቆጥቦ ሰንብቷል፡፡ በርካታ ውዝግቦች ሲሰሙበት የነበረው የክለቡ ቦርድ ከበጀት አመዳደብ ጋር በተያያዘ ያስቀመጠው መመሪያ በክለቡ የነበሩ ነባር ተጫዋቾችን አላረካ በማለቱ በቡድኑ ውስጥ ወሳኝ የነበሩ አምስት ተጫዋቾችን ወደ ተለያዩ ክለቦች መሸኘቱ ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የክለቡ ወዳድ እና ደጋፊዎች ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በተለያየ መልኩ በገለፁት የተቀውሞ ድምፅ የተነሳ የክለቡ የበላይ አካላት በዛሬው ዕለት ባደረጉት ውይይት የተነሳባቸውን ከፍተኛ ተቃውሞ ለማርገብ ወደ ሥራ መግባት ጀምረዋል፡፡ በዚህም መሠረት በክለቡ የነበሩ ሦስት ተጫዋቾች ውላቸውን ለማራዘም ስምምነት እንደፈፀሙ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል፡፡

የቡድኑ ሁለተኛ አምበል እና ከ2008 ጀምሮ በመስመር አጥቂነት እና ተከላካይነት ክለቡን ሲያገለግል የነበረው ያሬድ ዳዊት፣ በወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም የተጫወተው እና በድሬዳዋ፣ ደቡብ ፓሊስ እና መከላከያ ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው የመስመር ተከላካዩ አናጋው ባደግ እንዲሁም የመሀል ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ ለተጨማሪ አመት በክለቡ ለመቆየት ቅድመ ስምምነት በዛሬው ዕለት ፈፅመዋል፡፡

ተጫዋቾቹን እየተነጠቀ መሆኑ የገባው ወላይታ ድቻ በትላንትናው ዕለት ለሀድያ ሆሳዕና ፊርማውን ያኖረውን አጥቂ ስንታየው መንግስቱን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን ምናልባትም የተጫዋቹ ውል በፍጥነት በሀድያ ሆሳዕና የማይፀና ከሆነ በድጋሚ በድቻ መለያ ልንመለከተው እንደምንችል ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችሁ ማጣራት ለማረጋገጥ ችላለች፡፡