መከላከያ ከከፍተኛ ሊጉ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል


በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመሩት መከላከያዎች በትናንትናው ዕለት የአራት ነባር ተጫዋቾችን ውል ያደሱ ሲሆን አሁን ደግሞ ሦስት ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ ክለብ በይፋ በአንድ ዓመት ውል የግላቸው አድርገዋል፡፡

ከትናንት በስትያ የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን እና ረዳቱን ዮርዳኖስ ዓባይን ውል በማራዘም እና ሁለት ተጨማሪ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን በመቅጠር የ2014 ዝግጅቱን የጀመረው መከላከያ የጃፋር ደሊል፣ አሌክስ ተሰማ፣ ዳዊት ማሞ እና ገናናው ረጋሳን ውል ያራዘመ ሲሆን ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊጉ በአንድ ዓመት ውል ማስፈረሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

ግብ ጠባቂው ሙሴ ገብረኪዳን ረዘም ካለ የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመልሰውን ዝውውር ፈፅሟል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክ ፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀድያ ሆሳዕና ግብ ጠባቂ ከተጠቀሱት ክለቦች በተጨማሪ ለበርካታ ቡድኖች ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊግ በምድብ ሀ ተደልድሎ በመጨረሻም መውረዱን ባረጋገጠው ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን በመጫወት ያሳለፈው ሙሴ በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ምርጫ ረዘም ካለ ጊዜ በኋላ በአንድ ዓመት ውል ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመልሰውን ዝውውር አጠናቋል፡፡

ሌላኛው አዲስ ተጫዋች ዳዊት ወርቁ ነው፡፡ በመሀል ተከላካይነት በደደቢት፣ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ደግሞ በወልድያ ከተማ በመጫወት አሳልፎ በድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በመመለስ ለጦሩ የአንድ ዓመት የውል ፊርማውን አስፍሯል፡፡

ሦስተኛው ፈራሚ ልደቱ ጌታቸው ሆኗል፡፡ እንደ ሁለቱ ፈራሚዎች ሁሉ በከፍተኛ ሊግ የሚጫወተው እና ዘንድሮ በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን አመቱን ያሳለፈው የመሀል ተከላካዩ ወደ መከላከያ በዛሬው ዕለት አምርቷል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና በቅርቡ ክለቡ በሸራተን ሆቴል ባዘጋጀው ሲምፖዚየም መከላከያ የሚለውን ስም መቻል በሚል ስያሜ ለመለወጥ በፕሮግራሙ ላይ በተነሳው ጥያቄ መሠረት በቅርቡ የክለቡ ቦርድ በሚያደርገው ስብሰባ የስያሜ ለውጡ እንደሚፀድቅ እና በቀጣዩም ዓመት ክለቡ በፕሪምየር ሊጉ በአዲሱ ስያሜው ሊጠራ እንደሚችል ከክለቡ አካባቢ ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጫ አግኝታለች፡፡