ትውልደ ኢትዮጵያዊው ተጫዋች በሊቨርፑል የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ውሉን ፈርሟል

በኢትዮጵያ የተወለደው ታዳጊው ተጫዋች መልካሙ ፍራውንዶርፍ በእንግሊዙ ሊቨርፑል ክለብ የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ኮንትራቱን ፈርሟል።

በከምባታ ጠምባሮ ዞን የተወለደው እና የእግርኳስ ህይወቱን በጀርመን የጀመረው መልካሙ ፍራውንዶርፍ ወደ እንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል እንዳመራ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። የ17 ዓመቱ የአጥቂ አማካይ ዓምና ከጀርመኑ ሆፈንየም ሊቨርፑል ከደረሰ በኋላም ከ18 ዓመት በታች ቡድኑ ጋር ጥሩ ብቃቱን ሲያሳይ ከርሟል። በተለይ በከተማ ተቀናቃኙ ኤቨርተን እንዲሁም በታዳጊዎች የኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ኢፕስዊች ታወን ላይ ያስቆጠራቸው ጎሎች ልዩ የብዙዎች ትውስታ ነበረች።

መለሰ የሚባል በሆፈንየም የሚጫወት ወንድም ያለው ተጫዋቹ በሦስቱም የአጥቂ ቦታዎች ላይ እንዲሁም በአጥቂ አማካይ ቦታ እንደሚጫወት ይታወቃል። በዘንድሮ የውድድር ዘመንም በ23 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን (አካዳሚ ውስጥ የሚገኙ እና እርሱ ካስቆጠራቸው የግብ ብዛት በላይ ያገቡት ተጫዋቾች አራት ብቻ ናቸው) እና 4 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል። ከዋናው ቡድን ጋር ለበርካታ ጊዜ ልምምድ ሰርቶ የሚያውቀው ተጫዋቹም በዛሬው ዕለት የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ኮንትራት መፈረሙን ዚስ ኢስ አንፊልድ ዘግቧል።