የሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት ተጀመረ

በሁለት ምድብ ተከፍሎ በአስር ክለቦች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው የሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት በአራት ጨዋታዎች ተጀመረ፡፡

ወደ 2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕራምየር ሊግ የሚያድጉ ስምንት ክለቦችን ለመለየት በሁለት ምድብ ተከፍሎ በአስር ክለቦች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት በአራት ጨዋታዎች የተጀመረ ሲሆን በድምሩ 26 ግቦችም ከመረብ አርፈውበታል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ በተካሄዱ የዛሬ ጨዋታዎች በመክፈቻ ጨዋታ በምድብ ለ የሚገኙትን ሁለቱ የደቡብ ክልል ክለቦች ወላይታ ዞን እና ሀላባ ከተማን አገናኝቶ ሀላባ ከተማ 3ለ2 በሆነ ውጤት በድል ሲጀምር ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው የከምባታ ዞን እና የአዲስ አበባው ፔንዳ ክለብ ጨዋታ በከምባታ ዞን 1ለ0 ተደምድሟል፡፡

ከሰዓትም ጨዋታዎቹ በሁለት መርሀግብሮች ቀጥለው እጅግ በርካታ ግቦችን አስመልክቶናል፡፡ ፍፁም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያለመመጣጠን ያልታየባቸው የሱሉልታ ከተማ እና የአለታ ቤዛ ውሀ ጨዋታ በሱሉሉታ ፍፁም ብልጫ 11 ለ 1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ የመጨረሻ የዕለቱ ጨዋታ የሆነው የአራዳ ክፍለ ከተማ እና የምስራቅ ክፍለ ከተማ ጨወታ በአራዳ 7ለ1 አሸናፊነት ተፈፅሟል፡፡