በአምላክ ተሰማ ሁለተኛ የኦሊምፒክ ጨዋታውን ይመራል

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በዳኝነት የወከለው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ለሁለተኛ ጊዜ ጨዋታ እንዲመራ ተመርጧል፡፡

በጃፓን አስተናጋጅነት በአንድ ዓመት ተራዝሞ እየተከናወነ የሚገኘው የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተለያዩ የስፖርት አይነቶች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በውድድሩም ላይ እየተከናወኑ ካሉ ውድድሮች መሀል በሁሉም ፆታ እግር ኳስ ይገኝበታል፡፡ ለዚህም ውድድር ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ኢትዮጵያን በመወከል የወንዶች እግር ኳስን በዳኝነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ውድድሩን በአራተኛ ዳኝነት የጀመረው እና ትናንት ስፔን አውስትራሊያን 1ለ0 ስትረታ በመሐል ዳኝነት የመራው በአምላክ ረቡዕ ሐምሌ 21 በጃፓን ሳይታማ ስታዲየም ጀርመን፣ አይቮሪኮስት፣ ሳውዲ አረቢያ እና ብራዚል ከሚገኙበት ምድብ አራት ምሽት 2፡00 የሳውዲ አረቢያ እና የብራዚልን ጨዋታ ለሁለተኛ ጊዜ በመሐል ዳኝነት እንዲመራ ተመርጧል፡፡

የበምላክ ረዳት በመሆን መሐመድ ኢብራሂም ከደቡብ ሱዳን፣ ጊልቨርት ቺሮይት ከኬንያ፣ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ የሲውዘርላንድ ዜግነት ያለው ሰርዳን ሚሎት ተመድቧል፡፡ ከፈረንሳይ እና ከፖርቹጋል የተመረጡ ሁለት ዳኞች ደግሞ የVAR ዳኞች መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡