ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ከዋንጫ ፉክክር ወደኋላ ቀርተዋል

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና 1-1 ተለያይተዋል።

በዕለቱ የመጀመሪያ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና ተገናኝተው ፈረሰኞቹ በ24ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ መድን 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ብሩክ ታረቀኝ እና አላዛር ሳሙኤልን አስወጥተው አማኑኤል ተርፉ እና ዳዊት ተፈራን ሲያስገቡ ነብሮቹ በአንጻሩ ሻሸመኔን 3ለ1 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ብሩክ ማርቆስ ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና ሳሙኤል ዮሐንስ ወጥተው ግርማ በቀለ ፣ ደስታ ዋሚሾ እና ፀጋአብ ግዛው በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካትተዋል።

09፡00 ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል የተሻለ ግለት የነበራቸው ሀዲያዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፊጮ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ባሻገረው ኳስ ግርማ በቀለ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

በኳስ ቁጥጥሩ ከፍተኛ ብልጫ በመውሰድ ተረጋግተው ለመጫወት የሞከሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንጻሩ 13ኛው ደቂቃ ላይ በተገኑ ተሾመ አማካኝነት ሙከራ ካደረጉ በኋላ 17ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አማኑኤል ተርፉ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው በረከት ወልዴ የመታው ኳስ የግብ ጠባቂው ንቁ አለመሆን ተጨምሮበት ግብ ሆኗል።

የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ መክተው በሚያገኟቸው ኳሶች የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ለማድረግ ሲታትሩ የነበሩት ነብሮቹ ተመስገን ብርሃኑ 24ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ከሞከረው እና 29ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ቀንሶት ማንም ሳይጠቀምበት ከቀረው ኳስ ውጪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ በቀሪ ደቂቃዎችም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይፈጠር አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደስታ ዋሚሾ እና ፀጋአብ ግዛውን አስወጥተው ሳሙኤል ዮሐንስ እና ኡመድ ዑኩሪን በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ማነቃቃት ሲችሉ 56ኛው ደቂቃ ላይም ሄኖክ አርፊጮ ከቅጣት ምት አሻግሮት በረከት ወልደዮሐንስ ሳይጠቀምበት በቀረው ኳስ የተጋጣሚን ሳጥን መፈተን ችለው ነበር።

 

ፈረሰኞቹ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ይኑራቸው እንጂ በማጥቃት እንቅስቃሴው እጅግ ተቀዛቅዘው ሲቀርቡ ይባስ ብሎም 65ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። በረከት ወልደዮሐንስ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተመስገን ብርሃኑ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ነብሮቹ በየነ ባንጃን በግርማ በቀለ ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ይበልጥ ማሳለጥ ሲችሉ ከዕረፍት መልስ በቀየሯቸው ሦስት ተጫዋቾች ቅንጅት ግብ አግኝተዋል። በየነ ባንጃ ያመቻቸለትን ኳስ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ሲመታው የባሕሩ ነጋሽን እጅ የጣሰው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ ሲመለስ ኡመድ ዑክሪ አግኝቶት መረቡ ላይ አሳርፎታል። በቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር ተደርጎ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ እና ያገኟቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማቸው ለአቻ እንዳበቃቸው ተናግረው ከዋንጫው ፉክክር ቅድሚያ ስለ ቀጣይ ጨዋታ እንደሚያስቡ ሲጠቁሙ የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው አጀማመራቸው ጥሩ ቢሆንም ቀስ በቀስ በተለይም በማጥቃት እንቅስቃሴው ክፍተት እንደታየባቸው ገልጸው ከዕረፍት መልስ ያደረጓቸው ቅያሪዎች የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እንደረዳቸው በመናገር የሳሙኤል ዮሐንስን በተለያዩ የጨዋታ ቦታዎች የመጫወት ብቃት አድንቀዋል።