መረጃዎች| 102ኛ የጨዋታ ቀን

የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል

አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በሰባት ነጥቦች ቢራራቁም በተመሳሳይ ወቅታዊ አቋም የሚገኙ ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ማራኪ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በሰላሣ ስምንት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ያለመሸነፍ ጉዟቸው ለማስቀጠል እንዲሁም አሸንፈው ደረጃቸው ለማሻሻል እያለሙ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታመናል።

አዳማዎች ሽንፈት ከቀመሱ አራት ጨዋታዎች ማስቆጠራቸው እንደ አንድ ጠንካራ ጎን የሚነሳላቸው ጉዳይ ቢሆንም በቀደመው የማጥቃት ጥንካሬያቸው አሉ ለማለት ግን አያስደፍርም። ዘጠኝ ግቦች በማስቆጠር የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ኃላፊነት ተሸክሞ የነበረው ዮሴፍ ታረቀኝ ካጡ በኋላ የግብ ማስቆጠር አቅማቸው የተገደበው አዳማዎች ባለፈው አራት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት የግብ መጠን ሦስት ብቻ ነው። ቡድኑ ከሽንፈት በራቀባቸው አራት ሳምንታት በሦስቱም ግቡን ሳያስደፍ በመውጣት ያሳየው መሻሻል ግን በቅርብ ሳምንታት ከታዩ ጠንካራ ጎኖች ዋነኛው ነው።

በሰንጠረዡ ወገብ ባለው ተቀራራቢ የነጥብ ልዩነት ምክንያት ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል ያለው አዳማ የዴንማርክ ቆይታው አጠናቆ የተመለሰው የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዮሴፍ ታረቀኝ ግልጋሎት ማግኘቱም ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው። ከቀናት በፊት ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋቹ በጨዋታው የሚኖረው ተሳትፎ በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ለውጥ ማምጣቱ አያጠያይቅም።

በሰላሣ አንድ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ባለፉት ስምንት ሳምንታት ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ከስጋት ቀጠናው ተደላድለው እንዲወጡ አስችሏቸዋል፤ በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ ይዘው የሚወጡ ከሆነም የደረጃ መሻሻል ከማስመዝገብ በዘለለ በቀጣይ ወደ ሰንጠረዡ መሀከል ሊጠጉ የሚችሉበት ዕድል ያሰፋላቸዋል።

ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጉት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ሰባ ሦስት ያክል ደቂቃዎች የጠበቁት ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታው ከወትሮ የተዳከመ የማጥቃት አጨዋወት ነበራቸው። ከሳጥን ውጭ በተሞከሩና ከቆሙ ኳሶች ዕድሎች የፈጠረው ቡድኑ በዕለቱ በቁጥር ጥቂት ሙከራዎች ከማድረጉም በተጨማሪ በተጋጣሚ ሳጥን አደጋዎች መፍጠር አልቻለም። በነገው ዕለት ደግሞ በብዙ መለክያዎች የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት የገነባውና ከመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ያላስደፈረው ቡድን ስለሚገጥሙ የፊት መስመር ጥንካሬያቸውን መልሰው ማግኘት ግድ ይላቸዋል።

ቡድኑን በተረከቡበት የመጀመርያ ሳምንታት ለመከላከል ልዩ ትኩረት የሚሰጥ አቀራረብ፤ በቅርብ ሳምንታት ደግሞ በአንፃራዊነት የተሻለ የማጥቃት ሀሳብ ያለው ቡድን ያስመለከቱን አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እንደተጋጣሚው ሁኔታ የሚቀያይር የጨዋታ መንገዳቸው በነገው ጨዋታ ተገማች እንዳይሆኑ ይረዳቸዋል።

በአዳማ ከተማ በኩል ለሙከራ ወደ ዴንማርክ አቅንቶ የነበረው ዮሴፍ ታረቀኝ የተመለሰ ሲሆን በነገው ዕለትም ስብስቡ ውስጥ እንደሚኖር ሲጠበቅ የተቀሩትም የቡድኑ አባላትም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል። ሲዳማ ቡናዎችም በተመሳሳይ ከሁለት ጨዋታዎች ቅጣት መልስ የጊት ጋትኩት ግልጋሎት ያገኛሉ።

ሁለቱ  ቡድኖች ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው 25 ጊዜያት ሲዳማ ቡና 9 አዳማ ከተማ ደግሞ 6 ጊዜ ድል ሲቀናቸው 10 ጨዋታዎች በአቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታተቻው ሲዳማዎች 22 አዳማዎች ደግሞ 21 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የጨዋታ ሳምንቱ መዝግያ መርሀ-ግብር የተመለከቱ መረጃዎች

ቀድሞ ጨዋታውን ያከናወነው ወልቂጤ ከተማ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን የማጥበብ አለፍ ብሎም ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ወርቃማ ዕድል ያገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች አሸንፎ ሁለት ደረጃዎች ለማሻሻል ከሚያልመው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ።

በውድድር ዓመቱ ሁለት ድሎች ብቻ ያስመዘገበው ሻሸመኔ ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካት ደካማ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ባደረጉት ጨዋታ እጅግ የተሻሻለ የማጥቃት አጨዋወት የነበረው ቡድኑ በጨዋታው በርከት ያሉ ዕድሎች መፍጠር ቢችልም የአፈፃፀም ክፍተቱ፣ መዘናጋትና የግል ስህተቶች ዋጋ አስከፍሎታል። በጨዋታው ያሳዩት የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴና ከስድስት ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ ያስቆጠሩት ግብ ግን በአወንታ የሚነሳላቸው ጉዳይ ነው።

ቡድን የተሻለ ብልጫ ባሳየበት ጨዋታ ላይ በታየበት መዘናጋት ግብ ማስተናገዱ ከነገው ጨዋታ በፊት አስተካክሎት ለመምጣት የሚያስበው ድክመቱ እንደሆነ ይታመናል፤ የተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና የፊት መስመር ጥንካሬም ቡድኑ በተሻለ አኳኃን የኋላ ክፍሉ እንዲያደራጅ የሚያስገድደው ሌላው ምክንያት ነው።

ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወላይታ ድቻን አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ሁለት ደረጃዎች እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ቡድኑ ወደ ድል መንገድ ከመለሰ ወሳኝ ጨዋታ ማግስት በሊጉ ሁለተኛውን በርካታ ሽንፈቶች ካስተናገደ ቡድን ጋር መገናኘቱ መጠነኛ እፎይታ የሚሰጠው ይመስላል። ቡናማዎቹ የጦና ንቦቹን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ እጅግ የተጋለጠ የመከላከል አደረጃጀት ነበራቸው፤ አሰልጣኙ በቅርብ ሳምንታት በተደጋጋሚ የተስተዋሉት ዋጋ የሚያስከፍሉ የመከላከል ስህተቶች ማረም ቀዳሚ የቤት ስራቸው ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል። በተለይም ለግቦች መቆጠር መነሻ እየሆነ ያለው የላላው መስመሮችን የመከላከል አቅማቸው ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው የቡድኑ ክፍተት ነው።

ተጋጣሚያቸው ከግብ ጋር መራራቁ ሲታይ የተከላካይ ክፍላቸው ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ሊጠበቅ ቢችልም ሻሸመኔዎች በመጨረሻው ጨዋታ ባሳዩት ትጋትና የማጥቃት መንፈስ ወደ ጨዋታው ከቀረቡ ግን ለወትሮ ተጋላጭ የሆነው የቡናማዎቹ የመከላከል አደረጃጀት መፈተኑ አይቀሪ ነው። ከዚ በተጨማሪ በወሳኙ የንግድ ባንክ ጨዋታ ድንቅ እንቅስቃሴ አድርጎ በመጨረሻው መርሀ-ግብር ፈታኝ የማጥቃት አደጋዎች ያልፈጠረው የፊት መስመራቸው ጥምረት ወደ ተለመደው አስፈሪነቱ መመለስ ይኖርበታል።

ሻሸመኔ ከተማዎች አቤል ማሞም በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም፤ ወደ ሀገሩ ተጉዞ የነበረው ግብ ጠባቂው ኬን ሰይዲ ግን ቡድኑን ተቀላቅሏል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው በአራት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና አንድ ጨዋታ አሸንፎ የተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ቡናማዎቹ ሦስት ሻሸመኔ ከተማዎች በበኩላቸው ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችለዋል።