ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ላይ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ወስዷል

በዕለቱ ቀዳሚ በነበረው መርሃግብር አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡናን 2-1 በመርታት ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበትን ወሳኝ ድል አሳክተዋል።

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለወጥ ሱራፌል ዓወልን በቦና ዓሊ ተክተው ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ በአንፃሩ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ አራት ለውጦች ያደረጉ ሲሆን በዚህም አንተነህ ተስፋዬ ፣ አቤኔዘር አስፋው ፣ ቡልቻ ሹራ እና ማይክል ኪፖሮልን አሳርፈው በምትካቸው ጊትጋት ኩት ፣ ደስታ ዮሀንስ ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን እና ይገዙ ቦጋለን ለዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።

በከፍተኛ ዝናብ ታጅቦ ጅማሬውን ባደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በማለዳው በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ የመጀመሪያዋ ግብ ተቆጥራለች ፤ በ2ኛው ደቂቃ ጀሚል ያዕቆብ ፍቅሩ ዓለማየሁ ያደረሰውን ግሩም ኳስ ተጠቅሞ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ መስዑድ መሀመድ በግሩም አጨራረስ በማስቆጠር አዳማን መሪ አድርጓል።

ምንም እንኳን አስቀድመው ግብ ቢያስተናግዱም ሲዳማ ቡናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉ ነበሩ ፤ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ግን በጥቂት ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ አደጋ ለመደቀን ሲሞክሩ ተስተውሏል።

የአዳማዎች በዚህ አካሄድ በ20ኛው ደቂቃ ፍቅሩ ዓለማየሁ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ መክብብ ደገፉ በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ ሳጥን ውስጥ የነበረው ቢኒያም አይተን ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር የአዳማን መሪነት ማሳደግ ችሏል።

ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱም በኃላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች ረዘም ያለውን ጊዜ በአዳማ የሜዳ አጋማሽ ቢያሳልፉም ጥራታቸውን የጠበቁ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ውስንነቶች የታዩባቸው ሲሆን በንፅፅር በፈጠሯቸው የተሻሉ ዕድሎች ላይ የተጫዋቾች ግለኝነት ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።

30ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው የመሀል ተከላካይ አህመድ ረሺድ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ከሳጥን ውጭ ያደረገውን ሙከራ ለመከላከል ባደረገው ጥረት ባስተናገደው ጉዳት መነሻነት በታዬ ጋሻው ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

በ44ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናዎች ጥረት ፍሬ አፍርቶ ወደ ጨዋታ የተመለሱበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ ይገዙ ቦጋላ ላይ አቡበከር ሻሚል ላይ በሳጥኑ ጠርዝ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ደስታ ዮሀንስ በቀጥታ መቶ በማስቆጠር አጋማሹ በአዳማ ከተማ የ2-1 መሪነት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሶስት አውንታዊ የተጫዋቾች ቅያሬን በማድረግ የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በአጋማሹ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ጥራታቸው ከፍ ያሉ ዕድሎችን እንደ መጀመሪያው ሁሉ ለመፍጠር ተቸግረዋል ፤ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች እንደ መጀመሪያው ሁሉ በመልሶ ማጥቃት የመጫወት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ነቢል ኑሪ እንዲሁም 72ኛው ደቂቃ ላይ በቦና ዓሊ አማካኝነት ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጭ ወደፊት በመድረስ አደጋ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ73ኛው ደቂቃ ግን የጨዋታውን መልክ ሊቀይር የሚችል ክስተት ተመልክተናል ፤ ሲዳማ ቡናዎች ወደ አዳማ የሜዳ አጋማሽ በረጅሙ የጣሉትን ኳስ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ለማግኘት የጣረው የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ ኳስ በእጅ ነክቷል በሚል በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ የተሰናበተ መሆኑን ተከትሎ አዳማዎች ቀሪውን ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል።

የነበራቸውን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች ተረጋግተው ተጋጣሚን ለማስከፈት ከመሞከር ይልቅ ከፍተኛ ጥድፊያ የተሞላው የማጥቃት ጨዋታቸው የአዳማን የመከላከል መዋቅር በሚገባ ለመፈተን ሳይችል የቀረ ሲሆን አዳማዎች በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፈው ላለመስጠት ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቶ ጨዋታው በአዳማ ከተማዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሰሯቸው ሁለት ስህተቶች እና ሁለተኛው አጋማሽ በአጨራረስ ረገድ የነበረባቸው ድክመት ዋጋ እንዳስከፈላቸው ገልፀው በቀጣይ ጨዋታ ተሽለው እንደሚቀርቡም ገልፀዋል በአንፃሩ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ጨዋታው ከባድ እንደነበረ ገልፀው በዋነኝነት የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ደጋፊውን ከቡድኑ ለመነጠል ጥረት ስለማድረጋቸው ገልፀው ዳኞች ለውሳኔዎች ባይቸኩሉ የሚል ምክራቸውንም ለግሰዋል።