ባዬ ገዛኸኝ በመጨረሻም ወዴት እንዳመራ ታውቋል

ከባህርዳር ከተማ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እየቀረው ለሁለት ክለቦች በመፈረሙ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው አጥቂ በመጨረሻም ማረፊያው ተለይቷል፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በብዙሃኑ ዘንድ አነጋጋሪ ድርጊት ፈፅሞ ነበር። ይህም ተጫዋቹ በባህር ዳር ከተማ በ2014 የሚያቆየው ውል እያለው የልቀቁኝ ደብዳቤን አስገብቶ በመጠባበቅ ላይ እያለ ለሰበታ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና የሁለት ዓመት ውል መፈረሙ ነበር፡፡ ሁለቱም ክለቦች ተጫዋቹን የግላችን አድርገናል በማለትም ቡድኖቹ በሚገኙበት ክልል ተጫዋቹ የፈረመበትን ውል በተመሳሳይ ጊዜ ያፀድቃሉ፡፡ ምንም እንኳን አንድ ተጫዋች መፈረሙ የሚረጋገጠው በፈረመው ውል ብቻ ሳይሆን የግድ ከነበረበት ክለብ የመልቀቂያ ደብዳቤን ማቅረብ የሚገባው ስለነበረ በጣና ሞገዶቹ ቤት ውል ያለው ተጫዋች ያስገባው የልቀቁኝ ደብዳቤ እስኪቀበል ለሰበታ ከተማ? ወይንስ ለሀድያ ሆሳዕና ውሉን ህጋዊ ያደርጋል የሚለው ጉዳይ በውል ሳይለይ ቀናቶች ተቆጥረው ነበር።

ይሁን እንጂ ተጫዋቹ ያስገባውን ደብዳቤ ያጤነው ክለቡ በይፋ በስምምነት ከተጫዋቹ ጋር ከሰሞኑ መለያየቱ እርግጥ የሆነ ሲሆን ተጫዋቹም የመልቀቂያ ደብዳቤውን ለሀድያ ሆሳዕና በመስጠት መዳረሻው ሀድያ ሆሳዕና መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ በዚህም ባዬ ገዛኸኝ ለቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዓመታት የነብሮቹን መለያ በመልበስ ክለቡን የሚያገለግል ይሆናል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ከ15 ተጫዋቾች ጋር በተገናኘ በእግድ ላይ የሰነበተው ክለቡ ለመጨረሻ ጊዜ በተጫዋቾቹ የተከሰሰበትን የጥቅማጥቅም ጉዳይ ለመፈፀም የፊታችን ማክሰኞ ቀጠሮ መያዙን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡