መከላከያ የሁለት ተጫዋቾችን ውል አራዘመ

በቢሾፍቱ ከተማ ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ትናንት የጀመረው መከላከያ የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል፡፡

ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ሰመረ ሀፍታይ ውሉ ተራዝሞለታል፡፡ በትግራይ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጋቢት ወር ላይ ወልዋሎን ከለቀቀ በኃላ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ተሳታፊ መከላከያ በማምራት የስድስት ወራት ቆይታን አድርጓል፡፡ ጦሩ ከ ምድብ ሀ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ጦሩ እንዲመለስ የራሳቸውን ድርሻ ከተወጡት መሀል አንዱ የሆነው ይህ ተጫዋች ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ውሉ ተራዝሞለታል፡፡

ሌላኛው ውል ያራዘመው ተጫዋች ተከላካዩ ኢብራሂም ሁሴን ነው፡፡ የቀድሞው የሼር ኢትዮጵያ፣ ሰበታ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ኤሌክትሪክ ተጫዋች ዘንድሮ ለመከላከያ የከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ጉዞ ጥሩ ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን እሱም እንደ ሰመረ ሁሉ ለተጨማሪ ዓመት ውሉ በክለቡ ታድሶለታል፡፡