የሙጂብ ቃሲም ቀጣይ ማረፊያ ታውቋል

አነጋጋሪው የሙጂብ ቃሲም ዝውውር አሁን ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ መልክ ይዟል። ወደ አልጄሪያ ሊያደርግ የነበረው ዝውውር እክል የገጠመው ሙጂብ ቃሲም ወደ አዲስ ክለብ ለማምራት ተስማምቷል።

ባለፉት ሦስት የውድድር ዘመናት በፋሲል ከነማ ከመሐል ተከላካይነት አንስቶ በሒደት በፊት አጥቂነት አስደናቂ ጊዜያትን ያሳለፈው ሙጂብ ቃሲም በክረምቱ የዝውውር መስኮት በአልጄሪያ ሊግ ተካፋይ ወደሆነው ጄ ኤስ ካቢሌ የሚያደርገው ዝውውር እክል እንደገጠመው ከተረጋገጠ ወዲህ ቀጣይ ማረፊያው የት ይሆናል የሚለው ጉዳይ ሲያነጋግር ቆይቷል።

የቀድሞ ክለቡ ፋሲል ከነማን ጨምሮ ሰበታ እና ድሬዳዋ ከተማ የተጫዋቾችን ግልጋሎት በቀጣይ ዓመት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቢቆይም የሙጂብ ቃሲም የመጨረሻው ማረፊያ ድሬዳዋ ከተማ መሆኑ ታውቋል። በአሁኑ ሰዓት ዝውውሩን ለማጠናቀቅ በፌዴሬሽን እንደሚገኝም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።