“በአዲስ ክለብ ጠብቁኝ” – ሙጂብ ቃሲም

ከአልጄሪያው ክለብ ጋር የሚያደርገው ዝውውር ያልተሳካው ሙጂብ ቃሲም በወቅታዊ ጉዳይ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳቡን አጋርቷል።

ሙጂብ ወደ አልጀርሱ ክለብ ለማምራት ቢያስብም በተለያዩ ምክንያቶች ዝውውሩ ሳይሳካ መቅረቱን ዛሬ አረጋግጠናል። ይህን ተከትሎ በክለቡ በኩል ሙጂብ ከፋሲል ከነማ ጋር አብሮ እንደሚቆይ እና ሕጋዊ ሰነድ እንዳላቸው ከሰዓታት በፊት ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዮት ብርሀኑ ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፃቸውን ዘግበንላቹ ነበር። በሙጂብ በኩል ምን አይነት አቋም ይንፀባረቃል ስንል ተጫዋቹን አናግረን ተከታዩን ሀሳብ አጋርቶናል።

” የአልጄሪያው ክለብ ዕድል ሲመጣ ከክለቡ አመራሮች ጋር በመነጋገር ለሁለት ዓመት የተከፈለኝን ሙሉ ብሩን መልሼ አስፍላጊውን ነገር ሁሉ በማድረግ ህጋዊ መልቀቂያ ወስጃለው። ከአምስት ቀን በፊት የአልጄሪያው ጉዞ 80% እንደማይሳካ እየተረዳሁ ስመጣ ደጋፊዎችን ስለምወድ እና ስለማከብር ለክለቡ ሰዎች እንድንነጋገር ጥያቄ አቅርቤ ነበር። ሆኖም አንዳቸውም አመራሮች ምላሽ ሊሰጡኝ አልቻሉም። ይህ ደግሞ ምን ነገረኝ በፋሲል ከነማ እንደማልፈለግ አወቅኹ። ከዚህ የተነሳ ከተለያዩ ክለቦች ጋር መደራደር ጀምሬ አለው። ተመልሼም ወደ ፋሲል የሚሄድበት አግባብ የለም። ከፋሲል ከነማ የተለያየሁበትን ህጋዊ የሆነ መልቀቂያ ወስጃለው። ለፌዴሬሽኑም ውል ማፍረሻ ከፍያለው። ስለዚህ እኔ አሁን የማንም አይደለሁም። ነፃ ሆኜ ቁጭ ያልኩ ተጫዋች ነኝ። በቀጣይ በሀገራችን አዲስ ክለብ ጠብቁኝ። ከህግ ውጭ ባለ ነገር ተስማምቷል በማለት ሊመልሱኝ አይችሉም።”