የሲዳማ ቡና የህክምና ባለሙያው ውዝግብ…

“…የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከስራ የታገዱ መሆኑን እንገልፃለን” ሲዳማ ቡና

“የቃልም ሆነ የጽሁፍ ማስጠንቀቂ ሳይሰጠኝ ያለ አግባብ ከስራዬ መታገዴ ተገቢ አይደለም” አበባው በለጠ

አበባው በለጠ ከአስር ዓመታት በላይ ሲዳማ ቡናን በህክምና ባለሙያነት(ወጌሻ) አገልግሏል። በ2012 መጨረሻ ላይ ለሁለት ዓመት የሚያቆየውን ውል አራዝሞ አሁን ላይ ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት የሚቀረው አበባው ክለቡ “አስቀድሞ ባደረገው የውል ማጣራት የእርሶ ውል ህጋዊነት ያልተከተለ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። በመሆኑም የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከስራ የታገዱ መሆኑን እንገልፃለን” በሚል በፃፈው ደብዳቤ እግድ ተላልፎበታል።

በአንፃሩ የህክምናው ባለሙያ አበባው በለጠ በበኩሉ “ያለምንም በቂ ምክንያት የቃልም ሆነ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ ያለ አግባብ ከሥራ ገበታዬ ማንሳቱ ተገቢ አይደል። እስከ 2014 መጨረሻ ድረስ ቀሪ ኮንትራት እያለኝ ክለቡ ያለ አግባብ ያገደኝ በመሆኑ እስከ ኮንትራቴ ማብቂያ ድረስ ደሞዜ እንዲከፈለኝ” ሲል ለፌዴሬሽኑ ባስገባው የክስ አቤቱታ ደብዳቤ ገልጿል።

በሁለቱ አካላት የተፈጠረውን አለመግባባት ፌዴሬሽኑ በመመልከት በቅርቡ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።