መከላከያ ጋናዊ ተጫዋች አስፈርሟል

ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ ከተማ የምናውቀው ተጫዋች ጦሩን መቀላቀሉ ተረጋግጧል።

በአሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ የሚመሩት መከላከያዎች አዳዲስ ተጫዋቾችን በመቀላቀል ከትናንት በስትያ በቢሾፍቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እንደጀመሩ ዘግበን ነበር። አሁን በተገኘ መረጃ ደግሞ ክለቡ ጋናዊውን የተከላካይ አማካይ ኢማኑኤል ላሪያን በአንድ ዓመት ውል ማስፈረሙን ያመላክታል።

2010 ላይ ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል በማምራት ለድሬዳዋ ከተማ ለአንድ ዓመት ተጫውቶ የነበረው ኢማኑኤል ላሪያ ከብርቱካናማዎቹ ጋር ከተለያየ በኋላ ወደ ጃፓን ተጉዞ ነበር። ጋና ሶከር ኔት እንደዘገበው ከሆነ የቀድሞ የሀርትስ ኦፍ ኦክ ተጫዋች ከጃፓኑ ኦኮሲያ ኪዮቶ ከተባለው ክለብ ጋር ከስምንት ወራት በፊት ከተለያየ በኋላ ያለ ክለብ ተቀምጦ እንደነበር ያመላክታል። አሁን ደግሞ ለረጅም ዓመታት በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ ሲጠቀም የነበረው ነገርግን ከዓምና ጀምሮ የውጪ ተጫዋቾችን መጠቀም የጀመረውን መከላከያን መቀላቀሉ ተረጋግጧል።