አዲስ አበባ ከተማ በዋና አሠልጣኙ ዙርያ ውሳኔ አስተላልፏል

በቅርቡ አዲስ ቦርድ ያዋቀረው የመዲናይቱ ክለብ ከሰሞኑ ሲያደርግ በነበረው ጥልቅ ግምገማ የመቀጠል እና ያለ መቀጠሉ ነገር እርግጥ ያልነበረው የአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጉዳይ ዙርያ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ አሸናፊ በመሆን ወደ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉ ይታወሳል፡፡ ቡድኑን እየመራ ወደ ሊጉ በመመለሱ ረገድ ደግሞ ግንባር ቀደሙን ቦታ አሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ይወስዳል፡፡ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገ በኋላ ያለፉትን ወራት ከሌሎች የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች አንፃር በተጫዋች ዝውውርም ሆነ ከአሠልጣኙ ጋር የመቀጠሉ አልያም አዲስ አሠልጣኝ የመሾሙ ጉዳይ ላይ ዝምታን መምረጡን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ዘገባዎችን ስታቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ተቀዛቅዞ የከረመው ክለቡም ከሰሞኑ አዲስ ቦርድ በማዋቀር ወደ ስራ የገባ ሲሆን አዲሱ ቦርድም ጥልቅ ውይይቶችን ካለፈው አርብ ጀምሮ እስከ ዛሬ ምሽት ድረስ በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ በዋናነት ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደጉ ረገድ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው አሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ከክለቡ ጋር ይቀጥላል ወይንስ አይቀጥልም የሚለው ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ ሆኖ ለብዙሃኑ ጥያቄ ሆኖ የከረመ ቢሆንም አሁን እስማኤል አቡበከር እንዲቀጥል መወሰኑን እና ተጨማሪ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ለማካተት መወሰኑን ስራ አስኪያጁ አቶ ነፃነት ታከለ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ከአሰልጣኙ ጋር መቀጠሉ እርግጥ የሆነው አዲስ አበባ ከተማ ከነገ ጀምሮ ወደ ዝውውሩ ጎራ እንደሚል ስራ አስኪያጁ የጠቆሙ ሲሆኑ ወደ ሌላ ክለብ ያመራ የክለቡ ነባር ተጫዋቾችን በድጋሚ ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርጉም ነግረውናል፡፡ ቦርዱ ከእነኚህ ውሳኔዎች በተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያን ከዋናው ቡድን አንስቶ በሴቶች እና ከ20 አመት በታች ቡድኑ ላይም ማድረጉን ሀላፊው ጨምረው ነግረውናል፡፡