የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን በባህር ዳር ስታዲየም ልምምድ ሰርቷል

በነገው ዕለት ከፋሲል ከነማ ጋር ከነገ በስትያ ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርገው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከጨዋታዎቹ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል።

በኳታር አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ የምድብ ጨዋታዎች ከፊቱ የሚጠብቀው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ በትናንትናው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ይታወቃል። እግር መንገድ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከመስከረም 2 ጀምሮ የሚያደርገው ፋሲል ከነማም ቡድኑን ለመግጠም ያቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቶ ፋሲል ከነማ እና የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ነገ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ጠዋት ዘግበን ነበር።

ማረፊያውን በኦሊቭ ሆቴል ያደረገው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድኑም ዛሬ ከ9 ሰዓት ጀምሮ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምድ መስራቱን በስፍራው ተገኝተን ተመልክተናል። በአሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ የሚመራው ስብስቡም ለ1:25 ደቂቃዎች የቆየ ተግባር ተኮር ልምምድ ሲሰራ ነበር። በዋናነት ደግሞ አሠልጣኝ ሚቾ ተጫዋቾቻቸው ከኳስ ጋር ዘለግ ያለ ጊዜ እንዲያሳልፉ እየመከሩ ልምምዱ ሲሰራ እንደነበር ታዝበናል።

ፍጥነት የታከለበት የኳስ ቅብብል ከታየበት የቡድኑ ልምምድ በኋላ ደግሞ የማጣቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ተናበው እየተቀባበሉ ወደ ጎል ሊደርሱ የሚችሉበት ስልጠና ሲሰጥ ነበር። መጨረሻ ላይ ደግሞ ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ የሙሉ ሜዳ ግጥሚያ ሲያደርግ አይተናል። 10:25 ሲልም ቡድኑ ቀጣይ ልምምድ በስታዲየሙ ለመስራት ለመጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሜዳውን አስረክቦ ወጥቷል።