ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኬንያ ላይ የመጀመሪያ ልምምዱን ሰርቷል

በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴካፋ ዞን የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር ለማከናወን ወደ ኬንያ ከተጓዘ በኋላ ዛሬ የመጀመሪያ ልምምዱን ሰርቷል።

በቀጣይ ዓመት በግብፅ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የዞኑን የማጣሪያ ጨዋታዎች ለማድረግ በትናንትናው ዕለት ወደ ኬኒያ የተጓዘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ረፋድ 4 ሰዓት ላይ ልምምድ መስራቱ ታውቋል። ወደ ስፍራው ያቀኑት 21 ተጫዋቾችም ለአንድ ሠዓት ከሠላሳ ደቂቃዎች የቆየ ቀለል ያሉ የልምምድ ሥራዎችን በጂምካና የመለማመጃ ሜዳ እንደሰሩ ተመላክቷል።

ስብስቡ ልምምድ ከመስራቱ ከአንድ ሰዓት በፊት ደግሞ ባረፈበት ፌር ቪው ሆቴል የኮቪድ-19 ምርመራ እንደተደረገለት ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ከነገ በስትያ ከውድድሩ አስተናጋጅ ሀገር ክለብ ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ የሚያደርገው ቡድኑም በተመሳሳይ ነገ ረፋድ ሁለተኛ ልምምዱን በጂምካና የመለማመጃ ሜዳ እንደሚሰራ ተጠቁሟል። በአጠቃላይ 28 የልዑካን ቡድን ይዞ የተጓዘው ክለቡም ምንም አይነት የጉዳት ዜና እንደሌለበት ተጠቁሟል።

የንግድ ባንክ ጨዋታዎች

ነሐሴ 23 – ኢት/ንግድ ባንክ ከ ቪሂጋ ኩዊንስ 

ነሐሴ 26 – ኢት/ንግድ ባንክ ከ ኒው ጄኔሬሽን

ነሐሴ 28 – ኢት/ንግድ ባንክ ከ ዬይ ጆይን ስታርስ