ኢንስትራክተር አብረሀም መብራቱ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ዳሬ ሰላም ያቀናሉ

በታንዛኒያ ለሚገኙ ኢንስትራክተሮች የሚሰጠውን ስልጠና ለመስጠት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ወደ ስፍራው ያመራሉ፡፡

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) በስሩ ካሉ ጥቂት ኤሊት ኢንስትራክተሮቹ መካከል ኢትዮጵያዊው አብርሀም መብራቱ ይጠቀሳሉ፡፡ በሀገራችንም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ለአሰልጣኞች የላይሰንስ ስልጠናን በመስጠት የሚታወቁት አዲሱ የባህርዳር ከተማ አሰልጣኝ በያዝነው ሳምንት ደግሞ የመጀመሪያው ኢንስትራክተሮችን የሚያሰለጥን ኢትዮጵያዊ በመሆን ወደ ዳሬሰላም ያመራሉ፡፡ ከአስራ አራት ቀናት በፊት ከኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ ቀጥሎ ሁለተኛው ኢትዮጵያ በመሆን በላይቤሪያ ለሚገኙ 75 አሰልጣኞች የማሻሻያ የኤ፣ ቢ እና ሲ ስልጠናን በመስጠት የተመለሱት ኢንስትራክተሩ በታንዛኒያ ለሚገኙ የአሰልጣኞች አሰልጣኝ (ኢንስትራክተርነት) ስልጠና እንዲሰጡ ተመድበዋል፡፡

” ኢንስትራክተሮችን ለማሰልጠን በመመረጤ ለእኔም ሆነ ለሀገሬ ትልቅ ነገር ነው። በላይቤሪያ የነበረኝ ጊዜ የተሳካ በመሆኑ ካፍ ይሄን ስልጠና እንድሰጥ መርጦኛል። አሰልጣኞችን ከማሰልጠን አልፌ ኢንስትራክተሮችን ወደ ማሰልጠኑ መምጣቴ እንደ ሀገር ሊያኮራን ይገባል። እኔም ጥሩ ጊዜ እንደሚኖረኝ አምናለሁ።” በማለት ለድረገፃችን ገልፀውልናል።