የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን 7 ተጫዋቾችን ቀንሶ ዝግጅቱን ቀጥሏል

በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ዝግጅቱን አጠናክሮ ሲቀጥል 7 ተጫዋቾችንም መቀነሱ ታውቋል።

ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የ2022 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከፊቱ የማጣሪጣ ጨዋታዎች የሚጠብቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ላይ ማከናወን ከጀመረ ቀናቶች ተቆጥረዋል። በቅድሚያ ለ40 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረበው ቡድኑም ከባንክ ጋር አህጉራዊ የክለብ ውድድር ያለባቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች ስብስቡን ሳይቀላቀሉ የቀሩ ተጫዋቾችን ሳይዝ 31 ተጫዋቾችን በማግኘት ልምምድ ሲሰራ ቆይቷል።

ከቀናት በኋላ ከሩዋንዳ ጋር ላለበት የደርሶ መልስ ጨዋታ በቶሚ ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ ዝግጅቱን የቀጠለው ብሔራዊ ቡድኑም ሰባት ተጫዋቾችን መቀነሱ ተገልጿል። በፖስፖርት ምክንያት ከስብስቡ እንደተቀነሰች የተነገረውን የሀዋሳ ከተማዋ ሲሳይ ገብረዋህድን ጨምሮ በሻዱ ረጋሳ (አዲስ አበባ ከተማ)፣ ንግስት አስረስ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ መዓዛ አብደላ (ቦሌ)፣ ኤልሳቤት ብርሃኑ (መከላከያ) እንዲሁም ማክዳ ዓሊ እና ሄለን መሰለ (አቃቂ ቃሊቲ) ከስብስቡ ወጥተዋል።

ከ31 ተጫዋቾች ሰባቱን የቀነሰው ቡድኑም በትናንትናው ዕለት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጠራቸውን ስድስት ተጫዋቾች ማግኘቱ ተመላክቷል። ይህንን ተከትሎም በአሁኑ ሰዓት 30 ተጫዋቾች ልምምዳቸውን እየሰሩ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና ነገ ረፋድ 4 ሰዓት ላይ በኢንጅነሪን ሜዳ ከቢሾፍቱ 17 ዓመት በታች የወንዶች ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ መያዙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ከነገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ በኋላ ደግሞ አሠልጣኝ ፍሬው ለሩዋንዳው የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚጠቀሟቸውን ተጫዋቾች የመጨረሻ ዝርዝር ይፋ እንደሚያደርጉ ሰምተናል።