የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የዛሬ ውሎ

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ሲከናወን ጅማ አባ ጅፋር መከላከያን ሲረታ ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበበ ከተማን አሸንፏል።

መከላከያ 1-3 ጅማ አባ ጅፋር

የመጀመርያዎቹን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሁለቱ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በጅማ አባ ጅፋር አሸናፊነት ተጠናቋል። ገና በመጀመርያ ደቂቃዎች ደጋግመው በመሐመድ ኑሩ እና ዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት ወደ ጎል መድረስ የጀመሩት ጅማዎች ብዙም ሳይቆዩ የተገኘውን የማዕዘን ምት በመጠቀም ዳዊት ፍቃዱ በ11ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ኤርሚያስ ኃይሉ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥኑ አጥብቦ በመገባት የመታው ጠንካራ ኳስ ግብጠባቂው ዮሐንስ በዛብህ እንደምንም ያዳናት ኳስ በመከላከያ በኩል ተጠቃሽ ሙከራ ከመሆኗ ውጭ የተዘበራረቀ እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። ጅማዎች በበኩላቸው ጎሉን ካገኙ በኃላ አስቀድሞ በነበራቸው ወደ ጎል የመድረስ ፍጥነት እየተቀዛቀዘ ቢመጣም አልፎ አልፎ የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ወደ ዕረፍት መዳረሻ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ በጥሩ ሁኔታ ከመሐል ሜዳ አንስቶ እያደራጀ የሄደውን ኳስ ዳዊት ፋቃዱ ነፃ አቋቋም ለሚገኘው መሐመድ ኑር ለመስጠት ያሰበውን ገናነው ረጋሳ ለማውጣት ሲሞክር በራሱ ላይ ጎል በማስቆጠር የጅማን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመርያ አጋማሽ ሁሉ በፍጥነት ወደ ጎል መድረስ የቻሉት ጅማዎች ከሳጥን ውጭ በመሐመድኑር ናስር አማካኝነት ግሩም ጎል አግኝተዋል። መሐመድ በተከታታይ በሦስቱም ጨዋታዎች ሦስት ጎል በማስቆጠር ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየተፎካከረ ይገኛል።

ያልተደራጀ እንቅስቃሴያቸውን አስተካክለው ያልመጡት መከላካያዎች ቢንያም በላይ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ እና ከቆሙ ኳሶች ጎል ፍለጋ ከሚያደርጉት ጥረት ውጭ የረባ ነገር ማስመልከት አልቻሉም። ሆኖም የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር የጅማዎች እንቅስቃሴ መዳከሙን ተከትሎ በተወሰነ መልኩ መነቃቃት ጀምረው ተቀይሮ በገባው ሠመረ ሃፍታይ በ65ኛው ደቂቃ ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

ጨዋታው በዚህ ተጠናቀቀ ሲባል ለመከላከያ ማስተዛዘኛ የሆነች ሙከራ ኤርሚያስ ኃይሉ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን በግንባር በመግጨት ቢመታውም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በዚሁ እንቅስቃሴ የቀጠሉት መከላካዮች በተጨማሪ ደቂቃ ከማዕዘን ተሻግሮ በተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ቢንያም በላይ ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት በመምታት የማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥሯል። ቢንያም በላይ ለመከላከያ በተከታታይ በሦስት ጨዋታ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በመፎካከር ላይ ይገኛል።

ጨዋታውም በጅማ አባ ጅፋር 3-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ የጅማ አባጅፋሩ ዳዊት ፍቃዱ ለሁለተኛ ጊዜ ኮከብ ተብሎ በመመረጥ የዋንጫ እና የ12ሺህ ብር ሽልማት ከቀድሞ ዳኛ ጌታቸው ገብረማርያም እጅ ተቀብሏል።

ኢትዮጵያ ቡና 1-0 አዲስ አበባ ከተማ

ብዙም ትርጉም ያልነበረው ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቡና እና የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ተመልካቸ አልባ ሆኖ ተካሂዶ በቡና አሸናፊነት ተጠናቋል። ግልፅ የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት ሳንችልበት በተደጋጋሚ በሚቆራረጡ ኳሶች አሰልቺ ሆኖ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል። ይሄም ቢሆን በ29ኛው ደቂቃ በቡናዎች በኩል ኳስን መስሮቶ ለመጫወት በሚደረግ ቅብብሎሽ ውስጥ በረከት አማረ የሰራውን ስህተት ቢንያም ጌታቸው ነፃ ኳስ አግኝቶ ወደ ጎል መትቶ በተከላካይ ተደርቦ ሲመለስ በድጋሚ ፍፁም ጥላሁን ሳይጠቀምበት የቀረው በአዲስ አበባዎች በኩል ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

አዲስ አበባዎች በረጃጅም ኳሶች ቢንያም ጌታቸውን ትኩረት ያደረጉ ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል የቡናማዎችን የመከላከል እንቅስቃሴን ቢፈትኑም ጎል ለማስቆጠር ሲቸገሩ በአንፃሩ ቡናማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት የነበራቸው እንቅስቃሴ በሙከራ ያልታጀበ ሆኖ አልፏል።

በተወሰነ መልቁ መነቃቃት የተመለከትንበት ሁለተኛው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡናዎች በ68ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስመልክተውናል። ከቀኝ ወደ ግራ በማጥበብ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተን የቡናው ሀቢብ ዛኪር ያቀበለውን ኳስ እንዳለ ደባልቄ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ከጎሉ መቆጠር በኃላ የፈዘዘውን ጨዋታ ይነቃቃል ቢባልም ምንም የተለየ ነገር ሳንመለከትበት ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የኢትዮጵያ ቡናው ሮቤል ተክለሚካኤል ኮከብ ተብሎ በመመረጥ የዋንጫ እና የ12ሺህ ብር ሽልማት ከቀድሞ አሰልጣኝ ወርቁ ደርገባ እጅ ተበርክቶለታል።

አጠቃላይ የምድብ ሀ ጨዋታ ዛሬ መጠናቀቁን ተከትሎ አስቀድመው ያረጋገጡት ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ በግማሽ ፍፃሜው የሚገጥሙትን ቡድን ነገ የሚያውቁ ይሆናል።