የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች ከነገው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታቸውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ነገ የሚያደርጉት ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የ2022 የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ውድድር ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በሁለተኛ ዙር የማጣሪያ መርሐ-ግብር ከሩዋንዳ አቻው ጋር የተደለደለ ሲሆን ከቀናት በፊትም የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ አድርጎ አራት ለምንም አሸንፎ ተመልሷል። ከኪጋሊ መልስ ለነገው የመልስ ጨዋታ ሲዘጋጅ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑም ዛሬ ረፋድ የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።

 

ከረፋዱ 3 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው የቡድኑ የልምምድ መርሐ-ግብር በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የተከናወነ ሲሆን ለ75 ደቂቃዎች የቆየ ነበር። በልምምዱም ቀለል ያሉ እና ለነገው ጨዋታ ዝግጁ የሚያደርጉ ሥራዎችን አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ሲያሰሩ ነበር። ቡድኑ ውስጥ ከሚገኙት 20 ተጫዋቾች መካከል ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የግል ሀዘን ካጋጠማት ተከላካዩዋ ብዙዓየሁ ታደሠ ውጪ ሁሉም ተሳትፈዋል። ተጫዋቿም በአሁኑ ሰዓት ባህር ዳር ባለመገኘቷ ከነገው ጨዋታ ውጪ እንደሆነች ተጠቁሟል። በዛሬው የቡድኑ የመጨረሻ ልምምድ ላይም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና የሥራ-አስፈፃሚ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ተገኝተው ነበር።

እንደ ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ሁሉ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድንም ከአመሻሽ 10:10 ጀምሮ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምድ ሰርተዋል። ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ የቡድኑን ልምምድ (የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ልምምድ) ለመመልከት ብትጥርም የቡድኑ አሠልጣኞች ፍቃደኛ ባለመሆን ሳይሳካ ቀርቷል። የሆነው ሆኖ 9 የአሠልጣኝ ቡድን አባላት፣ 23 ተጫዋቾች እና 4 የአስተዳደር ሰዎችን በአጠቃላይ 36 የልዑካን ቡድን በመያዝ ከትናንት በስትያ ባህር ዳር የገባው ብሔራዊ ቡድኑም በአሁኑ ሰዓት በዲላኖ ሆቴል ማረፊያውን አድርጓል።