የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በመጀመርያ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለከትናቸው ዐበይት ተጫዋች ነክ ጉዳዮች እነሆ!

👉 በላይ ዓባይነህ በተከላካይነት

በዘመናዊ እግርኳስ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ቡድናቸው መከተል ከሚፈልገው የጨዋታ መንገድ መነሻነት የተለያዩ ሚናዎችን በብቃት እንዲወጡ ይፈለጋል። ከዚህም አንፃር እንደቀደመው ዘመን በአንድ የመጫወቻ ቦታ ላይ ከተወሰኑ ተጫዋቾች ይልቅ የተለያዩ ሚናዎችን መወጣት የሚችሉ ተጫዋቾች በገበያው ላይ የአሰልጣኞች ተቀዳሚ የዝውውር ኢላማ ሲሆኑ ይስተዋላል።

በሀገራችን እግርኳስ ውስጥ እንዲሁ በብዛት የሚስተዋል ባይሆንም አንዳንድ ተጫዋቾች ቡድናቸውን በተለያዩ ሚና ሲያገለግሉ ተመልክተናል ከቀደሙት ተጫዋቾች አዳነ ግርማ እንዲሁም ከአሁኑ ዘመን ደግሞ ተመስገን ደረሰን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ከሚና ለውጦች ጋር በተያያዘም ባለፉት ዓመታት ጎልቶ ይነሳ የነበረው ሙጂብ ቃሲም በአዳማ ከተማ እና በፋሲል ከነማ ከመሀል ተከላካይነት ተነስቶ ወደ አስደናቂ አጥቂነት የተቀየረበት ሂደት ብዙ ተብሎለታል። በዚህ የሚና ለውጥ ሂደት ውስጥ ይህን ሙከራ ቀድመው በአዳማ ከተማ ቤት ያሳዩን አሸናፊ በቀለ ዘንድሮ ደግሞ አንድ አዲስ ሙከራን እየተገበሩ እየተመለከትን እንገኛለን።

በቀደመ የእግርኳስ ህይወቱ በተለይ በትልቅ ደረጃ በተጫወተባቸው ድሬዳዋ፣ ወልዲያ እና አዳማ ከተማ ክለቦች ውስጥ በመስመር አጥቂነት አልያም በመስመር አማካይነት የምናውቀው በላይ ዓባይነህ በክረምቱ ወደ ጅማ አባጅፋር ካመራ ወዲህ በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ እንዲሁም በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ወቅት በመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ የአብስራ ሙሉጌታ ጋር ተጣምሮ እየተመለከትነው እንገኛለን።

ተጫዋቹ በአዲሱ ሚናው ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል። በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ያለው ዝግጁነት፣ የተከፈቱ የሜዳ ክፍሎችን ተመልሶ የሚዘጋበት መንገድ (Negative Sprint)፣ ሸርተቴዎቹ ከብዙ በጥቂቱ ተስፋ ሰጪ ሆነው ተመልከተናል። ምናልባት ቀጣዩ የሙጂብ ቃሲምን የሚና ለውጥ ታሪክ የሚጋራው በላይ ዓባይነህ ይሆን? ጊዜ መልስ ይኖረዋል…

👉 የውጭ ተጫዋቾች የሥራ ፈቃድ የመዘግየት ጉዳይ

በዘንድሮው ዓመት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከተካተቱ አዳዲስ ጉዳዮች መካከል የሊጉ ተካፋይ ክለቦች በስበሰስባቸው መያዝ የሚችሏቸውን የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ቁጥርን ሦስት እንዲሆን የሚገድበው ደንብ ይገኝበታል። በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ግን እነዚህን ሦስት ተጫዋቾችን ከሥራ ፈቃድ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

የሀዋሳ ከተማው ግብጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ፣ የጅማው ማላ ሮጀር፣ የድሬዳዋ ከተማዎቹ ማማዱ ሲዲቤ፣ አውዱ ናፊዩ፣ አብዱለጢፍ መሐመድን የሥራ ፈቃድ ወረቀታቸው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ባደረጓቸው የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ጨዋታዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

የሥራ ፈቃዳቸው በጊዜ አለመጠናቀቁን ተከትሎ የተለያዩ ምክንያቶችን ማቅረብ ቢቻልም በክለቦች ውስጥ ስላለው ደካማ የእግርኳስ አስተዳደር ግን ፍንጭ የሚሰጥ አጋጣሚ ነው። የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ሻጭ እና ገዢ ክለቦች እንዲሁም ከተጫዋቹ ጋር መግባባት ከተደረሰ በኃላ በፊፋ የዓለምአቀፍ የዝውውር ሰርተፍኬት (ITS) ምዝገባቸው ከተረጋገጠበት ቀን አንስቶ የአዲሱ ክለባቸው ተጫዋቾች መሆናቸው እየታወቀ ተጫዋቾች በሀገሪቱ ህገደንብ መሰረት ሜዳ ገብተው ለመጫወት ሆነ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚያስፈልጋቸው የሥራ ፈቃድ እና ሌሎች መሰረታዊ ወረቀቶች የሟሟላት ሂደቱ በዚህ ደረጃ የመጓተቱ ጉዳይ ግን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

የተጫዋቾቹ ዝውውር ከተጠናቀቀ የቆየ ቢሆንም በክለብ አስተዳዳሪዎች ቸልተኝነት የተነሳ የተጫዋቾቹ የስራ ፈቃድ ተንከባሎ ሊጉ ሊጀመር የሰአታት እድሜ እስኪቀር መንከባለሉ ብሎም ጨዋታ ሳምንቱ ተጀምሮ በመካከል በዓል በመሆኑ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸው እንደ ምክንያት ሲጠቀስ ከማድመጥ በላይ የሚያሳፍር ጉዳይ አይኖርም።

“እስከ አሁን የት ነበሩ?” የሚለውን ጥያቄ ለጠየቀ ሰው ክለቦቹ ለዚህ የተዝረከረከ አሰራራቸው ምን አይነት ምላሽ ይሰጡ ይሆን የሚለው ነገር ግን አጓጊ ነው።

👉 ፍቃዱ ዓለሙ ከአማራጭነት ወደ ተመራጭነት ?

ፋሲል ከነማ በ2013 የውድድር ዓመት የሊጉ ቻምፒዮን ሲሆን ሙጂብ ቃሲም ዋነኛ ፊት አውራሪው ነበር። አንድ የፊት አጥቂ ጥቅም ላይ የሚያውል የጨዋታ አደራደርን ይጠቀም የነበረው ቡድኑ ግዙፉን አጥቂ በቋሚነት ሲያሰልፍ ቆይቷል። በዚህ ቡድን ውስጥ የተሟላ ጤንነት ያልነበረው ሌላኛው ዘጠኝ ቁጥር ፍቃዱ ዓለሙ ብዙ ዕድል ባያገኝም ወሳኝ በነበሩ አንዳንድ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ላይ ዕድል ያገኝ ነበር። ለአብነትም በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ ፍፁም ቅጣት ምት ያስገኘበት ከሲዳማ ቡና ጋርም እንዲሁ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ያስቆጠረባቸው አጋጣሚዎች ፋሲልን ስድስት ነጥቦች ያስጨበጡ ነበሩ። በጥቅሉ ሲታይ ግን ተጫዋቹ በውድድር ዓመቱ ከተሳተፈባቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ሰባቱን ተቀይሮ በመግባት ነበር የተጫወተው።

ዘንድሮ ክለቡ ሙጂብን ቢያጣም ኦኪኪ አፎላቢን ማዘዋወር ችሏል። ይህም ከዓምናው በተመሳሳይ አኳኋን ኦኪኪን በዋነኝነት እየተጠቀመ ፍቃዱን በሁለትኛ ዕቅድነት ይይዘዋል የሚል ግምትን አሳድሯል። ሆኖም በመጀመርያው ሳምንት ኦኪኪ በጉዳት ከጨዋታ ውጪ ሲሆን ፍቃዱ ባገኘው የመሰለፍ ዕድል ሐት-ትሪክ በመስራት ቡድኑን ወደ አሸናፊ አድርጓል። ይህ በመሆኑ ዐምና ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥሙ በሁለት አጥቂ በመጠቀም ሙጂብ እና ፍቃዱን ሲያጣምሩ የታዩት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በቀጣይ ጨዋታዎች በተመሳሳይ አኳኋን የኦኪኪ እና ፍቃዱን ጥምረት ሊያሳዩን ይችላሉ የሚል ግምትን አሳድሯል። ይህ ከሆነ ዘንድሮ ከኋላ በሦስት ተከላካዮች ወደሚጀምር አደራደር የመጡት አሰልጣኙ ፊት ላይም ሌላ ለውጥ እንዲያደርጉ ሊያስገድዳቸው ይችላል።

ያም ሆነ ይህ በአዲስ አበባ ከተማ እና መከላከያ የሚያውቁት አጥቂያቸው ከቻምፒዮንነት በኋላ ባለው ከባዱ የውድድር ዓመት ቀኝ እጅ ሊሆናቸው እንደሚችል በመጀመሪያው ጨዋታ አሳይቷል። ሁኔታው በእርሱ ላይ ያላቸውን እምነት ደጋግመው ለሚገልፁት አሰልጣኙ ጥሩ የምስራች ሲሆን በምን ዓይነት መንገድ ይጠቀሙበታል የሚለው ጉዳይ ደግሞ ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል።

👉 የሰመረ ሃፍታይ የመከላከል አበርክቶ

በአሰልጣኝ ዩሀንስ ሳህሌ ስር በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን በወቅቱ ከነበረው የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ቡድን ካደጉ ተጫዋቾች መካከል የነበረው የአሁኑ የመከላከያ የመስመር አማካይ (አጥቂ) ሰመረ ሃፍታይ በሊጉ በወልዋሎ መለያ በግቦች የታጀበ አስደናቂ አጀማመር እንዳደረገ አይዘነጋም።

ዐምና ተጫዋቹ አሰልጣኝ ዮሐንስን ተከትሎ በከፍተኛ ሊጉ በመከላከያ መለያ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ አደርጎ ከቡድኑ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉ አይዘነጋም። ወደ ሊጉ ተመልሶም ከክለቡ መከላከያ ጋር ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታ አስደናቂ የነበረ የመከላከል አበርክቶ ለቡድኑም መስጠት ችሏል።

በመስመር አማካይነት ጨዋታውን የጀመረው ሰመረ በተለይ ቡድኑ ከኳስ ውጭ በሚሆንባቸው ቅፅበቶች በጥልቀት ወደ ኃላ እየተሳበ በመስመሮች በኩል ለማጥቃት ይሞክር የነበረውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቋረጥ እና ለመስመር ተከላካያቸው ገናናው ረጋሳ በቂ የመከላከል ሽፋን በመስጠት ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፏል። ተጫዋቹ በዚህ የመከላከል አበርክቶው ውስጥ በቀደመው ጊዜ ከተጫዋቹ ተመልክተነው በማነውቀው ከፍ ባለ የትኩረት ደረጃ እና አስደናቂ የሜዳ ላይ ትጋት ይህን ሲያደርግ ተመልከትናል።

👉 የሄኖክ አየለ መጠን ያለፈ የደስታ አገላለጽ

ድሬዳዋ ከተማ ወላይታ ድቻን በጨዋታ የመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ ባሸነፉበት ጨዋታ የግቧ ባለቤት የነበረው ሄኖክ አየለ የደስታ አገላለጽ የተለየ ነበር።

ረዘም ላሉ ዓመታት በጉዳት የታመሰ የእግርኳስ ጉዞን ያደረገው ሄኖክ በ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም በደቡብ ፖሊስ መለያ ራሱን ካስተዋወቀ ወዲህ በሀዋሳ እና በወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ዘንድሮ በድሬዳዋ ከተማ ቤት ቆይታን እያደረገ ይገኛል።

በድሬዳዋ ከተማ መለያ የመጀመሪያውን ይፋዊ ጨዋታውን ተቀይሮ በመግባት ባደረገበት እና መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሲቀር በወላይታ ድቻ ግብጠባቂ እና ተከላካዮች አለመግባባት መነሻነት ያገኛትን ኳስ ወደ ግብነት የቀየረው ሄኖክ ባልተለመደ መልኩ ደስታውን ሲገልፅ ታዝበናል። የተረጋጋ ስብዕና ባለቤት የሆነው ሄኖክ ለወትሮው ከሚታወቅበት የተረጋጋ የደስታ አገላለጽ ውጭ ባልተለመደ መልኩ ከፍ ባለ ስሜት ደስታውን ሲገልፅ ብሎም የማዕዘን መምቻ ላይ የሚቆመውን ፕላስቲክ እስከመስበር የደረሰ የተጋነነ የደስታ አገላለጽ አሰመልክቶናል።

👉 ዳዊት እስጢፋኖስ 8 ወይንስ 10?

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ብዙዎችን በሀሳብ ከሚከፋፍሉ (Polarizing) ተጫዋቾች መካከል አንዱ ዳዊት እስጢፋኖስ እንደሆነ ይታመናል። ሜዳ ላይ ባለው የጨዋታ ባህሪ፣ ከሜዳ ውጭ በሚሰጣቸው አስተያየቶች እና በብዙ መመዘኛዎቹ በአዎንታዊ ሆነ በአሉታዊ መንገድ ሊጉ ላይ ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ ተጫዋቾች ተርታ ይመደባል።

ታድያ ይህ ተጫዋች ኳስን በየትኛውም ጫና ውስጥ ሆነ ለመቀበል ያለው ዝግጁነት ሆነ ለቡድን አጋሮቹ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን በማቀበል ረገድ የተሻለ አቅም እንዳለው ይታመናል። ነገርግን ይህን የተጫዋቹን አቅም ይበልጥ ለመጠቀም አሰልጣኞች ተጫዋቹን በየትኛው ሚና መጠቀም አለባቸው የሚለው ጉዳይ ግን በጣም በትኩረት መታየት የሚገባው ጉዳይ ነው።

ጅማ አባ ጅፋር ሀዋሳ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ የመጀመርያ 40 ደቂቃዎች ዳዊት እስጢፋኖስ ከአጥቂ ጀርባ በ10 ቁጥር ሚና እንዲሁም መስዑድ መሐመድ ተስፋዬ መላኩን ቀይሮ መግባቱን ተከትሎ በሁለት 8 ቁጥሮች መጫወት ላሰቡት ጅማዎች ከሁለቱ ስምንት ቁጥሮች እንደ አንዱ በመሆን ተጫውቷል።

በዚህ ጨዋታ ተጫዋቹ እንዲወጣ ከተሰጡት ሁለት የተለያዩ ሚናዎች በመነሳት ሁለቱን አማራጮች በጥቂት ለማየት እንሞክር። አንደኛው ሀሳብ የተጫዋቹን የመጨረሻ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ የመስጠቱን አቅም ይበልጥ ለመጠቀም ለአጥቂዎች ቀርቦ እንዲጫወት ማድረግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለጨዋታው እንቅስቃሴ ይበልጥ ቀርቦ ከጥልቀት እንደሚነሳ የመሀል ሜዳ ፈጣሪ አማካይ አጠቃላይ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲወስን ማስቻል የሚሉት ሁለቱ አከራካሪ ሀሳቦች ናቸው።

በመጀመሪያው አማራጭ ተጫዋቹ ይበልጥ እራሱን ቆጥቦ የጨዋታውን ሒደት በሚወስኑ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፍ የሚያስችለው ሲሆን በተጨማሪነትም ቡድኑ ከፊት ጀምሮ ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ከፊት አጥቂው ጋር በመሆን የመጀመሪያውን የጫና ማዕበል (Pressing Wave) እንዲያስጀምር የሚያደርግ ነው። በሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ተጫዋቹ ለአጠቃላይ የጨዋታው እንቅስቃሴ ቀርቦ ኳሶችን እየተቀበለ እና እያቀበለ አጠቃላይ የጨዋታው ሒደት ላይ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ሁነኛ ሚና የሚሰጠው ነው በዚህ ውስጥም በአንዳንድ ጨዋታዎች በተለይ በሰበታ ከተማ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር ተጫዋቹ በ6 ቀጥር ሚና የቡድኑን የኳስ ምስረታ ለማሳለጥ የተጫወተባቸውን ጨዋታዎችን በዚሁ ስር መመልከት ተገቢ ይሆናል።

ነገርግን ተጫዋቹን በሁለቱም ሚናዎች በመጠቀም ውስጥ እንደ ቡድን ቡድኖች በማጥቃቱ በመከላከሉም የሚያገኙት ጥቅም እና ጉዳት እንዳለ ሆኖ ተጫዋቹ ግን ይበልጥ በነፃነት በኳሷ አንፃራዊ መገኛ መነሻነት ይበልጥ በእንቅስቃሴዎቹ ላይ ተሳትፎን ለማድረግ ካለው ፍላጎት አንፃር ይበልጥ በ8ቁጥርነት መጠቀሙ አሁን ባለው ሁኔታ የተሻለው አማራጭ ይመስላል።

👉 ተስፋን የሰጠው ሚኪያስ ካሣሁን

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ባለፉት ዓመታት በድሬዳዋ ከተማ መለያ አስደናቂ ጊዜያት ያሳለፈው በረከት ሳሙኤል ያጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ይህን ቦታ በምን መልኩ ይደፍኑታል የሚለው ጉዳይ ይጠበቅ ነበር።

እርግጥ በቦታው የቀድሞውን የሀዋሳ ከተማ እና ሰበታ ከተማውን የመሀል ተከላካይ መሳይ ጳውሎስን ቢያስፈርሙም ማን ያጣምረዋል የሚለው ጉዳይ ሌላኛው በድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ መስመር ላይ ይነሳ የነበረው ጥያቄ እንደነበር አይዘነጋም። ታድያ ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች የቡድኑ የእድሜ እርከን ቡድኖች ውጤት የሆነው ሚኪያስ ካሳሁን መልስ ይዞ ብቅ ሊል ይመስላል።

ወጣቱ ተከላካይ በድሬዳዋ ከተማ መለያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመርያ ተሰላፊነት በጀመረበት የወላይታ ድቻው ጨዋታ መልካም የሚባልን ብቃት አሳይቷል። እርጋታን ተላብሶ የሚጫወተው ተከላካዩ ከኳስ ጋር የማይቸገር እንዲሁም በመከላከሉ ወቅት ጠንካራ የመከላከል ብቃቱን ማሳየት ችሏል።

እርግጥ ለድሬዳዋ ከተማ ከላይ ላነሳናቸው ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ መልስ የመስጠቱ ጉዳይ በሂደት የሚታይ ቢሆንም እንደ አጀማመሩ ግን ድሬዳዋዎች ከዚህ ወጣት ተከላካይ ላይ አብዝተው ተስፋ እንዲያረጉ ያስገደደ የጨዋታ ዕለት አሳልፏል።

👉 የተጫዋቾቻን የሥነ ምግባር ጉዳይ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ላይ ተጫዋቾች አላስፈላጊ በሆነ ድርጊቶች በተለይም በእንቅስቃሴ መነሻ ያላደረጉ ነገርግን ከዳኞች ጋር በሚፈጠረ አላስፈላጊ ንትርኮች ካርዶችን መመልከት የተለመደ ጉዳይ ነው።

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሚነሳው ይህ የተጫዋቾች የዲሲፕሊን ግድፈት አምና በመጠኑ የተሻሻለ ቢመስልም ዘንድሮ ግን ገና ከወዲሁ የማገርሸት ምልክቶችን ማሳየቱ አሳሳቢ ነው።

በ2014 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ጨዋታዎችን ለተመለከት እና ጉዳዩን በአስተውሎት ለመረመረ ከአብዛኛዎቹ ካርዶች በስተጀርባ ያለው እውነታ እንቅስቃሴዎችን ለማቋረጥ ብሎም በተዘዋዋሪ ቡድን ተጠቃሚ ሊያደርጉ ከሚችሉ ታክቲካዊ ጥፋቶች ይልቅ ራስን ካለመግዛት የሚመነጩ ከዳኛ ጋር የሚደረጉ ሰጣገባዎች መሆኑን ላስተዋለ በሂደቱ ራስን ሆነ ቡድንን ከመጉዳት ባለፈ የሚገኝ አንዳች ጥቅም አለመኖሩን ደግሞ የተጫዋቾቻችን የስነ ምግባር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከታዩ አራት የቀይ ካርዶች መካከል ዳዊት እስጢፋኖስ በሀዋሳ በተሸነፉበት ጨዋታ ከተጠባባቂ ወንበር ሆኖ ኳስ አቀባይን በፕላስቲክ የውሀ ጠርሙስ ወርውሮ በመማታቱ እንዲሁም ረመዳን ናስር ባልተገባ ባህርይ በቀይ ካርድ የወጡበት አጋጣሚ እና ሌሎች ለቁጥር የሚታክቱ ያለአግባብ ተጫዋቾች የሚመለከቷቸው ቢጫ ካርዶች የዚህ አዝማሚያ ዳግም በሊጋችን ሊያገረሽ ይሆን የሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚፈልግ ነው።

👉 ቸርነት ጉግሳ በግራ የመስመር ተከላካይነት?

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወላይታ ድቻን ለቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ቸርነት ጉግሳ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገበት የሰበታ ከተማው ጨዋታ ለወትሮው ከምናውቀው የመስመር አማካይነት ሚና ውጭ ባልተለመደ መልኩ በግራ የመስመር ተከላካይነት ሲጫወት ለመመልከት ችለናል።

በወላይታ ድቻ በመስመር አማካይነት ዐምና አስደናቂ ብቃቱን ያሳየው ቸርነት ጉግሳ በግራ መስመር ተከላካይነት በተሰለፈበት የሰበታው ጨዋታ ከቡድኑ እንቅስቃሴ በጣሙን ተነጥሎ በቀደመው ደረጃ ጨዋታው ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ተቸግሮ ተስተውሏል። ተጫዋቹ በባህሪው ተጫዋቾች በአንድ ለአንድ ግንኙነት ፍጥነቱን ተጠቅሞ በማለፍ እንዲሁም የሚከፈቱ የሜዳ ክፍሎችን በአስደናቂ ፍጥነቱ በማጥቃት እና በፈጣን ሩጫዎች ሳጥን ውስጥ በመግባት የሚታወቀው ተጫዋቹ በአዲሱ ሚናው ያንን የቀደመው የማጥቃት ነፃነቱን መመልከት ሳንችል ቀርተናል።

እርግጥ በአሁኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስብ ውስጥ በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ነጥረው መውጣት የቻሉት የመስመር አማካዮች (አጥቂዎች) መገኛቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደመሆኑ የተወሰኑት በተጠባባቂነት ሊቀመጡ አልያም አንዳንዶቹ የሚና ሽግሽግ ሊያደርጉ እንደሚችል የሚገመት ነው። ቸርነት ካለው ታታሪነት አንፃር ለዚህ ሚና መታጨቱ ብዙም ባያስገርምም ተጫዋቹ ከአዲሱ ሚናው ጋር በምን መልኩ ራሱን አጣጥሞ የቀደመ የማጥቃት አቅሙን ተጠቅሞ ጨዋታው ላይ የተወሰኑ የመከላከል ስራዎችን ጨምሮ ይጓዛል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

በተያያዘም ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሠልጣኙን በሸራተን ሆቴል ባስተዋወቀበት ይፋዊ መግለጫ ወቅት ከጋዜጠኞች በተነሳ ጥያቄ የክለቡ ፀሃፊ በአቶ ነዋይ አዲሱ የውድድር ዘመን ወሳኝ የግራ መስመር ተከላካይ እናሳያለን የሚል ሀሳብ ሰጥተው ነበር። ታድያ ይህ ንግግራቸው ቸርነት ጉግሳን ማለት ይሆን እንዴ?

👉 ተጫዋቾች በአዲስ የፀጉር ቀለም

አዲስ የውድድር ዘመን ሲመጣ ተጫዋቾች ብቃታቸውን አሻሽሎ የተሻለ ተጫዋቾች ለመሆን ከሚያደርጉት ጥረት ባልተናነሰ በአዳዲስ ገፅታዎች ብቅ ለማለት የውበት ሳሎኖች መመላለሳቸው በእኛ ሀገር ብዙም ባይለመድም በውጭ ሀገራት ሊጎች የተለመደ አጋጣሚ ነው።

በሊጉ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት የድሬዳዋ ከተማዎቹ የክረምቱ አዳዲስ ፈራሚዎች እንየው ካሳሁን እና ጋዲሳ መብራቴ ለክለባቸው የመለያ ቀለም የቀረበ ብርቱካናማ ቀለም ፀጉራቸውን ተቀብተው የታዘብን ሲሆን በተመሳሳይ የአዳማ ከተማዎቹ ዮሴፍ ዮሐንስ ፀጉር ሙሉ ለሙሉ ቀይ ቀለም ሲያቀልም የቡድን አጋሩ አሜ መሀመድም እንዲሁ የተወሰነ የፀጉሩን ክፍሉን በቀይ ቀለም ዳበስ አርጎ ተመልክተናል።