ኢትዮጵያ በምትሳተፍበት ውድድር ላይ 5 የኤርትራ ተጫዋቾች ጠፍተዋል

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው የሴቶች የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ የሚካፈሉ 5 የኤርትራ ተጫዋቾች መጥፋታቸው ተነግሯል።

የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከጥቅምት 18 እስከ 30 ድረስ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተከናወነ ይገኛል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ሁለት ጨዋታዎችን አድርጎ በሰፊ የግብ ልዩነቶች አሸንፏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ የውድድሩ የበላይ አካል ሴካፋ ባወጣው መግለጫ አምስት የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከቡድናቸው መጥፋታቸውን ያመላክታል።

በትናንትናው ዕለት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 5-0 የተሸነፉት ኤርትራዎች ስማቸው ያልተገለፁት አምስቱ ተጫዋቾች ካረፉበት ጂንጃ ሆቴል ረፋድ ላይ ጠፍተውባቸዋል። ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ ለአካባቢው ፖሊስ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ሴካፋ፣ የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ፖሊስ ተጫዋቾቹን ለማግኘት እየሰሩ መሆኑም ተጠቁሟል።