ሪፖርት | ዋልያዎቹ ከጋና ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

በገለልተኛ ሜዳ ላይ ጋናን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤቱ ከሚያስፈልገው ተጋጣሚው የተሻለ ፍላጎት ያሳየበት ጨዋታ በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከደቡብ አፍሪካው ሁለተኛ ጨዋታ አንፃር ባደረጓቸው አምስት ለውጦች ፋሲል ገብረሚካኤልን በተክለማሪያም ሻንቆ ፣ ሱለይማን ሀሚድን በአስራት ቱንጆ ፣ ያሬድ ባየህን በምኞት ደበበ ፣ ሱራፌል ዳኛቸውን በሽመልስ በቀለ እንዲሁም አማኑኤል ገብረሚካኤልን በዳዋ ሆቴሳ በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል።

በጨዋታው ጅማሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመቅረብ ሲሞክር አልፎ አልፎ ከጋና ተጫዋቾች ኳስን በማስጣልም የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲሞክር ይታይ ነበር። ሆኖም 6ኛው ደቂቃ ላይ ጋናዎች በግራ በኩል ገብተው የሰነዘሩትን ፈጣን ጥቃት የዋሊያዎቹ ተከላካዮች ማራቅ ሳይችሉ ቀርተው አንድሬ አዩ እና እድሪሱ ሱሊማና ከቅርብ ርቀት አከታትለው ያደረጓቸው የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራዎችን ተክለማሪያም ሻንቆ በአስደናቂ ብቃት አድኖባቸዋል።

ዋልያዎቹ 8ኛው ደቂቃ ላይ በተሻለ ሁኔታ ወደ ጋና ሳጥን ሲቀርቡ አቡበከር ናስር ከግራ አቅጣጫ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። በቶሎ ወደ ሦተኛው የሜዳ ክፍል የመድረስ ምልክቶችን ማሳየት የጀመሩት ጋናዎች በሰነዘሩት ጥቃት ሪችሞንድ ያዶም በሳጥኑ መግቢያ ወደ ቀኝ ባደላ ቦታ ላይ ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘውን ቅጣት ምት አንድሬ አየው 22ኛው ደቂቃ ላይ በመምታት ጋናን መሪ ያደረግች ግብ ከመረብ አገናኝቷል።

ከግቡ በኋላ ጨዋታው የተሻለ ክፍት የመሆን እና ፈጠን ያለ እንቅስቃሴን የማሳየት መልክ ነበረው። በጋናዎች በኩል 26ኛው ደቂቃ ላይ ሱለይማና እድሪስ ከቀኝ መስመር ተከላካዮችን አታሎ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ሲወጣ ኢትዮጵያዊያኑ በዛው ደቂቃ በሰጡት ምላሽም ዳዋ ሆቴሳ ሳይታሰብ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ድኗል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በኢትዮጵያ በኩል 28ኛው እና 36ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ እና ሽመልስ በቀለ ከሳጥን ውስጥ በቀጥታ በመምታት ጌያነህ ከበደ ደግሞ 30ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑ በቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ በቁጥር ተመጣጥኖ በገባበት ቅፅበት ከአቡበከር ናስር የደረሰውን ኳስ በግንባር በመግጨት ሞክረዋል። ሦስቱም ሙከራዎች ኢላማቸውን ቢጠብቁም የደቡብ አፍሪካው ግብ ጠባቂ ዮሴፍ ወላኮትን የመፈተን አቅም ሊኖራቸው አልቻለም።

ከኳስ ውጪ በራሳቸው ሜዳ ላይ መቆየትን በመምረጥ በነጠቁበት ጊዜ ደጎ በድንገተኛ ጥቃት ወደ ዋልያዎቹ ግብ ክልል ይደርሱ የነበሩት ጥቋቁር ከዋክብቱም በጆርዳን አየው የርቀት ሙከራ ሲያደርጉ 41ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። ቡድኑ በግራ በኩል በፍጥነት የገባበትን የማጥቃት ሂደት ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ያገኘው ሪቻርድ ያዶህ ወደ ላይ ልኮታል።

የቀዳሚው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች የጨዋታ ምልልስ ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር አልቀጠለም። ጨዋታው ከዕረፍት መልስ በእንቅስቃሴ ፍጥነቱ ዝግ ብሎ የጀመረ ነበር። ቀዳሚው አደገኛ ሙከራም የታየው 57ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ሽመልስ በቀለ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። ጨዋታው ወደ ጋና አጋማሽ አዘንብሎ የቀጠለ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በየተራ ኳስ በመያዝ የቁጥጥር የበላይነትን ቢቀባበሉም የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ቆይተዋል።

በዚህ ሁኔታ የቀጠለው ጨዋታ 72ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝቷል። ጋናዎች ኳስ መስርተው ለመውጣት ሲጥሩ የመሀል ተከላካዩ ጆሴፍ አይዶ በአቡበከር ናስር በደረሰበት ጫና የተነጠቀው ኳስ በአቡበከር ፣ ጌታነህ እና መስዑድ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ሲደርስ ጌታነህ ከበደ ከአቡበከር ናስር የመጨረሻውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ተቀብሎ የአቻነታን ግብ ከመረብ አዋህዷል። ከግቡ በኋላ ጋናዎች ከቆሙ ኳሶች እና ከርቀት በቀጥታ በመምታት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ኢላማቸውን ሲጠብቁ አልታዩም። በኢትዮጵያ በኩል 89ኛው ደቂቃ ላይ ሦስት ለሁለት በሆነ የቁጥር ብልጫ በመልሶ ማጥቃት ወደ ጋና ሳጥን የደረሱበት አጋጣሚ በውሳኔ በመዘግየት ምክንያት ወደ ሙከራነት ሳይቀየር ቀርቷል። በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ጋናዎች ያገኙትን ቅጣት ምትም መጠቀም ሳይችሉ ጨዋታው በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።