የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 2-4 ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ እና ሰበታ ከተማ ካደረጉት የምሽቱ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም- ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው

” እንደ ወላይታ ድቻ ጨዋታውን ስናየው ይህንን ውጤት መያዛችን እና መሪ መሆናችን ጥሩ ነው፡፡ፕሪምየር ሊጉ ገና መጀመሩ ነው፡፡ መሪ መሆናችን ለፕሪምየር ሊጉ ዋስትና ሊሆነን አይችልም። ለእያንዳንዱ ጨዋታ ትኩረት በመስጠት እና ተጋጣሚያችንን እያከበርን እግርኳሱን እያከበርን መቀጠል ነው ያለብን። ስለዚህ ጊዜያዊ መሪ ሆንን እንጂ ከፊታችን ገና 25 ጨዋታ አለ። በዕለቱ ግን ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ለደጋፊዎቻች እና ተጫዋቾቻችን ጥሩ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከስንታየው የፍፁም ቅጣት ምት መሳት እና እስከ ምንይሉ የመጨረሻ ጎል ያሉ ክስተቶች

“እንደነገርኩህ እኔ ጀማሪ አሰልጣኝ አደለሁም። ብዙ ነገሮች አውቃለሁ። ከዛ ደግሞ ስንታየውን እናውቀዋለን። የስነ ልቦና ችግር እንዳይኖርም ጥሩ ነገር ሰርተናል። እና ዛሬ እንደ ቡድን ነው የተንቀሳቀስነው፡፡ እየመራን እየተመራን አቻ እየወጣን ፍ/ቅ/ም እየሳትን. . .  ብዙ ተለዋዋጭ ባህሪ ነበረው፡፡ የኛ አጨዋወታችን ደግሞ ጠቅሞናል። የክለቡ ፍላጎት የማሸነፍ ፍላጎት ነው። ሌሎች ችግሮች ውስጥ ሳይገባ ሁሉንም ነገር በጊዜ ማጠናቀቅ አለብን። ዞሮ ዞሮ አሁንም ክሬዲት ሊወስዱ የሚችሉት ተጫዋቾቼ ናቸው፤ ሁለተኛ ደግሞ ደጋፊዎቻችን ናቸው፡፡

አንተነህ ጉግሳ እና ደጉ ደበበ በሌሉበት ተክቶ ስለገባው ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ

“መልካሙ ዘንድሮ ሊጉ ከተጀመረ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ዛሬ የገባው። ብዙ ክፍተት አላየሁም ጥሩ ነበር። ቡድኑም እንዳለ እንደ አንድ ሆኖም ተጫውቷል፡፡ ስለዚህ ቀላል የሚባል ድል አይደለም፡፡

ስለ ቀጣዩ የፋሲል ጨዋታ

“እኛ እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ ጥሎ ማለፍ ነው የምናየው፤ የተለየ ዝግጅት አናደርግም። ሀምሳ ፐርሰንቱን የተጋጣሚያችንን አጨዋወት ተመልክተን እንመጣለን። እያንዳንዱ ጨዋታ የጥሎ ማለፍ እና የፍፃሜ ጨዋታ ነው፡፡ በሙሉ ልብ ለቀጣይ ጨዋታ ተዘጋጅተን እንመጣለን፡፡

ስለ ስንታየው ቀጣይ የፍፁም ቅጣት ምት መቺነት

“በቀጣይም ቢገኝ መቺያችን እሱ ነው፡፡ በተሳተ ቁጥር ከፔናሊቲ መቺነት የምናወጣ ከሆነማ በራስ መተማመናቸው እየወረደ ይመጣል እና መቼም የመጀመሪያ መቺያችን እሱ ነው፡፡

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሰበታ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ዛሬ በነበረው ጨዋታ ድቻዎች ይገባቸዋል፡፡ እንኳን ደስ አላችሁ ማለትም እፈልጋለሁ፡፡

ስለ ቡድኑ ቁልፍ ችግር

“ከዚህ ቀደም የነበረው የአግቢ ችግር ነበር የነበረው። የማስቆጠር አቅማችንም በጣም ደካማ ነው የነበረው። ነገር ግን በዛሬው ሁኔታ ሆነህ ደግሞ ስታየው ማስቆጠር ችለናል። ሆኖም የመከላከል አቅማችን ደግሞ ዛሬ ጥሩ አልነበረም። ለምሳሌ ዛሬ አንተነህ ከቅጣት መልስ ስለመጣ በእርግጥ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ሊከብድ ይችላል፡፡ ግን የመከላከል ሂደታችን ዝብርቅርቅ ያለ ነበር። የመሀል ክፍላችንም እንደ ቡድን እየተጫወተ አልነበረም። ስለዚህ ሙሉ ለሙሉ የተበላሸ ጨዋታ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡