ሪፖርት | የጦና ንቦቹ በምርጥ አጀማመራቸው ቀጥለው ወደ ሰንጠረዡ አናት ወጥተዋል

ድንቅ ሁለተኛ አጋማሽ ያስመለከተን የሰበታ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በድቻ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሰበታ ከተማ ከጉዳት እና ቅጣት የተመለሱለት ጌቱ ኃይለማሪያም እና አንተነህ ተስፋዬን እንዲሁም ፍፁም ገብረማሪያምን በታፈሰ ሰርካ ፣ ጁኒያስ ናንጄቤ እና ዘካሪያስ ፍቅሬ ተክቶ ጨዋታውን ሲጀምር ወላይታ ድቻ ሀብታሙ ቦጋለን ጉዳት ባገኘው ደጉ ደበበ ቦታ ተጠቅሟል።


ሰበታ ከተማ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዞ ጨዋታውን ጀምሯል። በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ተጋጣሚያቸው ከራሱ ሜዳ እንዳይወጣ ክፍተቶችን እየደፈኑ የጨዋታውን ፍሰት መሀል ላይ እንዲቀር አድርገዋል። ከሚነጥቋቸው ኳሶችም ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት አስፈሪ ምልክቶች ነበሩት። በዚህም 7ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች ከተከላካይ ጀርባ በተጣለ ኳስ ግብ ቢያስቆጥሩም አስቆጣሪው ቃልኪዳን ዘላለም በኃይለሚካኤል አደፍርስ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የዕለቱ አርቢትር ሀብታሙ መንግሥቴ ሽረውታል።


ከዚህም በኋላ የቡድኖቹ ፍልሚያ በሜዳው አጋማሽ ላይ ተገድቦ ሲቆይ የድቻዎች የሚሰነዝሩት ፈጣን ጥቃት ሌላ ዕድል ይዞላቸው መጥቶ ነበር። 23ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ሳሙኤል ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ እየገባ የነበረው ቃልኪዳን ዘላለም ላይ በሰራው ጥፋት ድቻዎች ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም የሥንታየሁ መንግስቱ ቄንጠኛ ምት ሳይሰምር በለዓለም ብርሀኑ በቀላሉ ድኗል።

አልፎ አልፎ ብቻ ኳስ ሲያንሸራሽሩ ይታዩ የነበሩት ድቻዎች በቁጥር ብዙ ባይሆኑም አስፈሪ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ የተሻሉ ሆነው በመቀጠል በቀጥተኛ ጥቃት ግብ አስቆጥረዋል። 33ኛው ዳቂቃ ላይ በረከት ወልደዮሐንስ ከኋላ ያሻማውን ኳስ ስንታየው ሲገጭለት ምንይሉ ወንድሙ ይዞ በመግባት ለስንታየሁ ለመመለስ ሲሞክር አንተነህ ተስፋዬ ለማውጣት አስቦ በራሱ ላይ በማስቆጠሩ ድቻ ቀዳሚ ሆኗል።


ወደ ፊት አጥቂው ፍፀም ገብረማሪያም መቅረብ ያልቻለው የሰበታዎች የኳስ ምስረታ ሂደት ከግቡ በኋላ በተሻለ መልኩ ወደ ድቻ ሜዳ መግባት ችሏል። 38ኛው ደቂቃ ላይም በረከት ወልደዮሐንስ ከመስመር የመጣን ኳስ ለማራቅ ሲሞክር በእጅ በመንካቱ ሰበታዎች ፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኙ በረከት ሳሙኤል አጋጣሚውን ወደ ግብነት ለውጦታል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታው ክፍት ሆኖ ሲታይ ሰበታዎች በተሻለ ሁኔታ ሳጥን ውስጥ ተገኝተዋል። 43ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች በአግባቡ ያላረቁትን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ ከሳጥን ውስጥ ሜክሮ ኳሱ ተጨርፎ ወደ ግብ ቢያመራም ፂዮን መርዕድ እንደምንም አድኖታል። ድቻዎችም በመልሶ ማጥቃት ግብ አፋፍ ቢደርሱም የምንይሉ ወንድሙ ጥረት ወደ ከባድ ሙከራነት ሳይቀየር ቀርቷል።


ጉሽሚያዎች በርከት ብለውበት የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ፍልሚያ ተጋግሎ ሲመለስ በቶሎ ጎል አስተናግዷል። ሰበታ ከተማዎች በቀኝ መስመር 50ኛው ደቂቃ ላይ ከሳሙኤል ሳሊሶ መነሻነት የሰነዘሩት ፈጣን ጥቃት በጌቱ ኃይለማሪያም ሲሻማ ፍፁም ገብረማሪያም በግንባር ገጭቶ አስቆጥሯል። ከዚህ በኋላ ሁለቱም የማጥቃት ፍላጎታቸው ጨምሮ እንቅስቃሴው ወደ ሳጥኖች እየተጠጋ ይታይ ነበር። ሆኖም ይታይባቸው የነበረው ጥድፊያ ጥረታቸው ወደ አስደንጋጭ የግብ ሙከራዎች እንዳይቀየር አድርጓል።


64ኛው ደቂቃ ወላይታ ድቻዎች ከቆመ ኳስ ግብ አስቆጥረዋል። የያሬድ ዳዊትን የቀኝ መስመር የቅጣት ምት ለፍፁም ቅጣት ምት ጎል መነሻ የነበረው በረከት ወልደዮሐንስ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ በማገናኘት ስህተቱን አካክሷል። ይህ ከሆነ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ድቻዎች ሦስተኛውን ግብ አግኝተዋል። ሳጥኑ አቅራቢያ ከክሪዚስቶም ንታንቢ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ቅብብል ያቋረጡትን ኳስ ስንታየሁ ሲያመቻችለት ቃልኪዳን ዘላለም አክርሮ በመምታት ከመረብ ዶሎታል። ተጫዋቹ አምና ለለበሰው የሰበታ መለያ ደስታውን ባለመግለፅ ያለውን ክብር ገልጿል። ድቻዎች መልሶ ማጥቃታቸው ይበልጥ ስል ሆኖ ደጋግመው ወደ ግብ ሲደርሱም ታይተዋል።


በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው የተተኮሰው ግለቱ ጋብ ቢልም ሰበታዎች ወደ ድቻ ሜዳ በሚገቡበት አጋጣሚ የጦና ንቦቹ በመልሶ ማጥቃት የሚወራወሩባቸው ቅፅበቶች መልሰው ያደምቁት ነበር። በዚሁ ሁኔታ በቀኝ መስመር ሰብረው የገቡበት አጋጣሚም 80ኛው ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ንጉሴ ሲመቻች ምንይሉ ወንድሙ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ በመምታት አራተኛ ግብ አድርጎታል። ሰበታዎች ተጨማሪ የማጥቃት ቅያሪዎችን አድርገው ጫና በመፍጠር ከመስመር በሚነሱ ኳሶች አደጋ ለመጣል ሞክረዋል። ያም ሆኖ ልየነቱን ማጥበብ ሳይችሉ አዝናኙ ጨዋታ ተቋጭቷል።

የጦና ንቦቹ ዛሬ ባስመዘገቡት አራተኛ ተከታታይ ድል የሰንጠረዡን አናት መቆናጠጥ ችለዋል።