ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ አሰልጣኞችን የተመለከቱ ጉዳዮች በዚህኛው ፅሁፍ የተካተቱ ናቸው።

👉 አሰልጣኞች ላይ እየተሰነዘሩ የሚገኙ ተቃውሞዎች

የየትኛውም ክለብ ደጋፊ ክለቡ እየሄደበት ያለው መንገድ ምቾት ባልሰጠው ጊዜ መቃወም በተቃራኒው ትክክል ነው ብሎ ሲያምን ደግሞ የማበረታታ ኃላፊነት አለበት። በሁለቱም ፅንፎች ግን ሀሳቦች የሚሰነዘሩበት መንገድ አግባብነት ባለው መንገድ መግለፅ እንዲሁም የክለቡን ጥቅም በማይፃረር መልኩ የመሆናቸው ነገርግን ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል።

የትኛውም አሰልጣኝ በቅድሚያ የሚዳኘው ሜዳ ላይ እያስመዘገበ በሚገኘው ውጤት መሆኑ ባያጠያይቅም ገና ከወዲሁ ግን የተለያዩ ቡድኖች ደጋፊዎች አሰልጣኞቻቸው ላይ በዚህ ልክ ተቃውሞ ሲሰነዘሩ መመልከታችን አስገራሚ ያደርገዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ ፣ ገብረመድህን ሀይሌ ፣ ዝላትኮ ክራምፖቲች ፣ አሸናፊ በቀለ ፣ ሙሉጌታ ምህረት ፣ መሳይ ተፈሪ ገና 5ኛ ሳምንቱ ላይ በሚገኘው የሊግ ውድድር በተለያዩ አጋጣሚዎች በክለባቸው ደጋፊዎች ተቃውሞን ሲያስተናግዱ ተመልክተናል።

ምናልባት በተቃውሞ አቅራቢ ደጋፊዎች ከአጠቃላይ የክለቡ ደጋፊዎች አንፃር ምን ያህሉ ናቸው የሚለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ የቴሌቪዥን ስርጭቱን ተከትሎ በወረቀት ላይ የሰፈሩ የእገሌ ልቀቅልን መልዕክቶች እየተለመዱ መጥተዋል።

ሌላኛው መነሳት የሚያስፈልገው ጉዳይ ከአንዳንዶቹ የተቃውሞ ድምፆች በስተጀርባ እግርኳሳዊ ያልሆኑ ፍላጎቶች ሲስተዋሉ እንመለከታለን ፤ ሊጉ ገና እንደጀመረ በ2ኛ እና 3ኛ የጨዋታ ሳምንት ተቃውሞዎችን መመልከት ከመጋረጃ በስተጀርባ እውን እነዚህ ተቃውሞዎች እግርኳሳዊ አመክንዮ አላቸው ወይ የሚለው ጉዳይ ትኩረትን የሚሻ ነው።

በተጨማሪም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ተቃውሞዎች ከልክ አልፈው ያስተዋልንባቸው አጋጣሚዎቹ ነበሩ። በዚህም ተጫዋቾች ሁሉ ከደጋፊዎች ጋር ግብግብ የገጠሙበትን አጋጣሚ ተመልክተናል። በመሆኑም ተቃውሞዎችም ሆነ ድጋፎች በልክ መሆን ካልቻሉ ክለቡን ከመጥቀማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝን ስለሚሆን ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል።

👉 የደምሰው ፍቃዱ ቀጣይነት?

ከአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጋር ገና በሊጉ ጅማሮ የተለያዩት አዲስአበባ ከተማዎች ሌላ አሰልጣኝ ለመቅጠር አማራጮችን እያጤኑ እንደነበር አይዘነጋም።

ቡድኑ አማራጮችን እስኪያጤን የሦስት ጨዋታ ዕድል የተሰጣቸው የቀድሞው የእስማኤል አቡበከር ረዳት እና የአሁኑ የቡድኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ የተሰጣቸውን ግዳጅ በአመርቂ ሁኔታ ተወጥተዋል።

የሊጉ የአምና አሸናፊ የነበሩትን ፋሲል ከነማን እና መከላከያ ከጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መርታት የቻሉት አዲስአበባ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ባያስተናግዱ ኖሮ ሦስተኛ ድላቸውን ለማሳካት ተቃርበው ነበር።

አሰልጣኝ ደምሰው ፍፁም ደካማ በሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ለተጋጣሚዎቹ እጅ የሰጠውን ስብስብ በፍጥነት በዚህ ደረጃ በማሻሻል ነጥቡን እንዲያሻሽል በማድረግ ጥሩ የሚባል ተግባርን መፈፀም ችለዋል። በመሆኑም የክለቡ አመራሮች ከዚህ መነሻነት በቋሚነት ሥራውን ይሰጧቸው ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 የመከላከል አጨዋወት

መከላከል እና ማጥቃት በእግርኳስ የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም። በመከላከል ሆነ በማጥቃት በሚደረጉ ሂደቶች ውስጥ እንደ ቡድን መንቀሳቀስ እጅግ ወሳኙን ሚና ይይዛል።

በሀገራችን ግን ያለው አረዳድ ከዚህ ጋር በተወሰነ የሚጣረስ ነው። መከላከል ለተወሰኑ የሜዳ ክፍል ተጫዋቾች እንዲሁም ማጥቃቱም በተመሳሳይ ለጥቂት የቡድን ተጫዋቾች የመስጠቱ ዝንባሌ በስፋት ይስተዋላል።

ነገርግን እግርኳስ የቡድን ጨዋታ እንደመሆኑ በማጥቃት ሆነ በመከላከል እንዲሁም በሁለቱ ሽግግሮች ወቅት እያንዳንዱ ሜዳ ላይ የሚገኝ ተጫዋች የሚወጣው ሚና እንዳለ መገንዘብ መሰረታዊው ጉዳይ ነው።

ከማጥቃት ጨዋታ ይልቅ የመከላከል እንቅስቃሴ ይበልጥ ተደጋጋሚ በልምምድ ሜዳ የሚሰሩ ሥራዎች ውጤት እንደሆነ ይታመናል። ለመከላከል መሰረታዊው ጉዳዮች ውስጥ የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾችን ሜዳ ላይ ማብዛት ወይንም በቁጥር በርከት ብሎ ወደ ራስ ሜዳ መሰብሰብ ሁለተኛ(Secondary) ጉዳዮች ናቸው።

መሰረታዊው የመከላከል እሳቤ ከተጫዋቾች አዕምሮ እንዲሁም ከአሰልጣኙ የጨዋታ ሀሳብ የሚመነጭ ነው። በአዕምሮ ረገድ ለመከላከል ዝግጁ የሆነ ቡድን ከኳስ ውጪ የሚያስፈልጉትን ሥራዎች ለመስራት በቂ የሆነ የአዕምሮ ዝግጁነት ላይ ተገኝቶ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ሌላኛው የአሰልጣኙ የጨዋታ እሳቤ ቡድኑ እንደቡድን ኳስ በሚያጣበት ወቅት በሜዳው የላይኛው ክፍል ኳስን ለማግኘት ይጫወታል ወይንስ ቶሎ ወደ መከላከል ቅርፁ በመግባት ይከላከላል ወይንስ ሌላ መንገድ አለው የሚሉ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ግለፅ የተቀመጠ እቅድ መኖር የመከላከልን ሥራን ለማቅለል ከፍተኛ ሚናን ይወጣሉ።

በመጨረሻም ሌላኛው ብዙም ሲተገበር የማንመለከተው ጉዳይ የ”Rest in Defense” አስተሳሰብ ነው። ይህም ቡድኑ በላይኛው የሜዳ ክፍል ኳስን ለማግኘት በሚጫወትበት ወቅት ለግባቸው ቀርበው የሚገኙ የመከላከል ተጫዋቾች ከተጋጣሚ ተጫዋቾች አንፃር የሚኖራቸውን አቋቋምን ይመለከታል። ይህም እንደቡድን ከመከላከል እሳቤ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሲሆን የቡድን አባላት በቁጥር በርከት ብለው በሰው ሜዳ በሚከላከሉበት ወቅት በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ የሚገኙ ተጫዋቾች ደግሞ ኳሱ ከጫና ወጥመዱ አልፎ ቢመጣ እንኳን ቡድናቸው በሽግግሮች ጉዳት እንዳይደርስበት ለመከላከል በሚያግዝ አቋቋም የተጋጣሚ ተጫዋቾችን ላይ ጫና የማሳደር እሳቤ በሚገባ ሲተገበር አይስተዋልም።

👉 የኢስማኤል አቡበከር ስታድየም መገኘት

አሰልጣኝ እስማኤል አበቡበከር ከቡድን መሪያቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት መነሻነት ከአዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኝነት ኃላፊነታቸው መነሳታቸው ሲታወስ ጉዳያቸውም በመደበኛ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።

በሁለቱ ግለሰቦች መካከል የተፈጠረውን ክርክር ዕልባት ለመስጠት ጉዳያቸው በሲዳማ ክልል በሚገኝ ችሎት እየታየ ሲሆን ከቀናት በፊት የመጀመሪያ ቀጠሯቸውን በፍርድ ቤት ተገኝተው የተሟገቱ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ለህዳር 24 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።

ታድያ በዚህ አጋጣሚ መነሻነት ዳግም ወደ ሀዋሳ ያቀኑት አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር የቀድሞ ቡድናቸው ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየበትን ጨዋታ በስታዲየም ተገኝተው የተከታተሉ ሲሆን በተመሳሳይ የቡድን መሪው አቶ ሲሳይ ተረፈም እንዲሁ ከዕድምተኞች መካከል ነበሩ።