መቋጫ ያላገኘው የኢያሱ ለገሰ ጉዳይ

ለጅማ አባ ጅፋር አስቀድሞ የፈረውና እና በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ውሉ የተጠናቀቀው ኢያሱ ለገሰ ውሳኔ ሳያገኝ የሦስት ሳምንት ጨዋታ አልፏል።

የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ጥቅምት ሠላሳ ከአዲስ አበባ ጋር ኮንትራቱ እንደሚያልቅ በማመን ቅድመ ስምምነት ከወራት በፊት ከጅማ አባጅፋር ጋር በማድረግ ከቡድኑ ጋር ቢሸፍቱ በመገኘት ቅድመ ዝግጅት አብሮ ሲሰራ ቆይቷል። ከጊዜ በኋላ ዳግመኛ ወደ ቀድሞ ክለቡ በመመለስ የሦስት ሳምንት ጨዋታዎችን የተጫወተው ኢያሱ ጥቅምት ሠላሳ ከአዲስ አበባ ጋር ያለው ኮንትራቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ውል ለማራዘም ወደ ፌዴሬሽን ቢያቀናም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ምክንያቱ ደግሞ በፌዴሬሽኑ ዘንድ እውቅና ያገኘ የውል ሰነድ ጅማ አባ ጅፋር ያቀረበ መሆኑን ተከትሎ ነው። ሆኖም ግን ጅማ አባ ጅፋሮች ፍቃደኛ ሆነው የቅድመ ስምምነቱን ውል የሚቀዱ ከሆነ በሚል ፌዴሬሽኑ የማግባባት ስራ ለመስራት ባሳለፍነው ዓርብ ቢሞክርም ጅማ አባጅፋሮች ”በፍፁም አንለቀውም እንፈልገዋለን። በፍጥነት ክለቡን የማይቀላቀል ከሆነ ቅጣት እናስተላልፍበታለን” የሚል አቋም አንፀባርቀዋል።

በዚህ መነሻነት አዲስ አበባዎች እያሱን የግላቸው እንዲሆን ከፌዴሬሽኑ ተገቢ የሆነ ምላሽ የማያገኙ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፊፋ ይዘው ለመሄድ እያሰቡ እንደሆነ እየገለፁ ይገኛል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያናገርነው ኢያሱ “በአሁን ሰዓት መጫወት የምፈልገው ለአዲስ አበባ ቢሆንም ከፌዴሬሽኑ ፍትህ አለማግኘቴ እንዳለ ሆኖ ጅማዎች ወደምፈልገው ክለብ በመሄድ እንድጫወት ቢፈቅዱልኝ ደስተኛ ነኝ። ያ ካለሆነ የሚሆነውን ተቀብዬ እቀጥላለሁ” ሲል ገልፆልናል።