ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ባህር ዳር ከተማ

የሊጉ ስድስተኛ ሳምንት መደምደሚያ የሆነውን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

የነገ ምሽቱ ጨዋታ ውጤት የማግኘት ግዴታ ውስጥ የሆኑ ቡድኖችን ያገናኛል ቢባል ማጋነን አይሆንም። እርግጥ ነው እስካሁን ምንም ነጥብ ያላሳካው ጅማ አባ ጅፋር ሳይረፍድበት የነጥብ ስብስቡ ቆጣሪ ስራ እንዲጀምር የማድረግ ግዴታ ውስጥ ይገኛል። ሆኖም ከተጋጣሚው የሰባት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኘው ባህር ዳርም ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች እንደመምጣቱ ለሦስተኛ ጊዜ ያለነጥብ ከሜዳ መውጣት ለዋንጫ ፉክክር የታጨውን ቡድን ግምት እጅግ የሚያወርድ መሆኑ አይቀሬ ነው።

ከውጤት ባሻገር ሁለቱ ተጋጣሚዎች እየታዩባቸው ያሉ ድክመቶች ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። በዚህ ውስጥ የሁለቱም ችግር ተደርጎ የሚወሰደው የቅንጅት ችግር ነው። ጅማ አባ ጅፋር በየጨዋታዎቹ የሚያደርጋቸው የአደራደር ለውጦች እና እነሱን ተከትሎ የሚታዩት የተጨዋቾች መቀያየር አለመረጋጋቱን ያሳያል። የሚጠቀማቸው የወጣት እና አንጋፋ ተጫዋቾች ስብስጥር በሚና እና በመሰለፍ ዕድል መለዋወጥ አሁንም ሲቀጥል አንዳንድ ጊዜ ፍፁም ያልተጠበቀ ሆኖ ይታያል። እንደ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የመጨረሻ የድህረ ጨዋታ ሀሳብ ግን መሻሻሎች እየታዩ ነው። ነገር ግን ቡድኑ ወጥ የሆነ ጠንካራ ጎንን እየገነባ ነው ብሎ ለመደምደም አስቸጋሪ ነው።

በባህር ዳር በኩልም ተመሳሳይ ችግር ይስተዋላል። እንደተጋጣሚው የጎላ የተሰላፊዎች መለዋዋጥ ባይታይበትም ቡድኑ በሚከተለው የኳስ ቁጥጥርን ባማከለ አጨዋወት ውስጥ የሚፈለገው የቅንጅት ደረጃ ላይ መድረስ አልቻለም። ይህ በመሆኑም በሁሉት ድሎች የጀመረው ባህር ዳር ተገማችነቱ እየጎላ ሲሄድ የስብስቡ ስብጥር በተለይም በተጋጣሚ ሜዳ ላይ በትዕግስት ኳስ ይዞ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያስቻለው ደረጃ ላይ አይገኝም። ያም ቢሆን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱም እንደነገ ተጋጣሚያቸው ሁሉ በሚከተሉት የጨዋታ ዓይነት መሻሻሎችን እያዩ እንደሆነ በአስተያየታቸው ጠቁመው ነበር።

ከአጨዋወት አንፃር ስንመለከተው ሁለቱም የመጨረሻ ተጋጣሚዎቻቸውን ዓይነት ቡድን ከመግጠማቸው ተነስተን የተወሰኑ ነጥቦችን መመልከት እንችላለን። እንደባህር ዳር ሁሉ ኳስ የሚይዘው ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው አባ ጅፋር ነገም ፈጣን መልሶ ማጥቃትን ዕቅድ አድርጎ እንደሚገባ ይገመታል። በዚህም ወደ ግራ መስመር ያደላ ጥቃቱ ሊጎላ የሚችል ሲሆን የቀጥተኛ ኳሶች አጠቃቀሙም በቁጥር ከፍ ማለቱ የሚቀር አይደለም። ሆኖም በመከላከሉ ረገድ ለተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች በተለይም ከተከላካይ መስመሩ ጀርባ የሚደርሱትን መቋቋም አለመቻሉ ከፊትም ከሥነ ልቦና ጋር የተያያዘ የሚመስለው የአጨራረስ ድክመቱ በነገው ጨዋታም ዕክል ሊፈጥርበት ይችላል።

ባህርዳር ከተማም እንደአምስተኛ ሳምንት ተጋጣሚው መከላከያ ሁሉ በጅማም ከመልሶ ማጥቃት ጋር የሚጋፈጥ ይመስላል። በዚህ ረገድ ቡድኑ የኳስ ምስረታውን ጥራት ማሻሻል እና ኳሶች መልሰው አደጋ በሚፈጥሩባቸው የሜዳ ክፍሎች ላይ እንዳይቋረጡበት መጠንቀቅ ያሻዋል። በቢኒያም በላይ የተቆጠረበት ግብም በመከላከል ቅርፁ ላይ ሶሆን የተጨዋቾች ትከረቱ ላይ መስራት ያለበት መሆኑን ያሳየ ነበር። የተሻሻለ ይመስል የነበረው የኋላ ክፍሉ ቀጥተኛ ጥቃቶችን ለማቋረጥ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል። በማጥቃቱ በኩል ግን በሜዳው ስፋት በቁጥር በርክቶ የሚከላከለውን የነገውን ተጋጣሚውን የሚያከፍቱ ቅብቅብሎች ከጥሩ የአጨራረስ ብቃት ጋር ሊኖረው የግድ ነው።

ጅማ አባ ጅፋር ጉዳት ላይ የሰነበቱት ሽመልስ ተገኛ እና እዮብ ዓለማየሁን እንዲሁ ቅጣት ላይ የሚገኘው ዳዊት እስጢፋኖስ ግልጋሎትን አያገኝም። በባህር ዳር በኩል በባለፈው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምድ ላይ ጉዳት የገጠመው ኦሴይ ማዉሊ እና በጉዳት ሜዳ ላይ ከታየ የሰነበተው ተመስገን ደረሰ እንዳገገሙ ሲታወቅ አምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ሰለሞን ወዴሳ ግን አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ሀብታሙ መንግሥቴ መሪነት ይከናወናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

-ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ከተገናኙባቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱን በአቻ ውጤት ሲያገባድዱ ጅማ አባ ጅፋት አንድ ጊዜ ድል አድርጓል። ጅማ አራት ባህር ዳር ደግሞ ሦስት ግቦችም አሏቸው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

አቡበከር ኑሪ

አህመድ ረሺድ – መናፍ ዐወል – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ ዲሳሳ

አብዱልከሪም ኒኪማ – አለልኝ አዘነ – ፍፁም ዓለሙ

ፉዐድ ፈረጃ – ኦሴ ማውሊ – ዓሊ ሱለይማን

ጅማ አባጅፋር (3-4-3)

ዮሐንስ በዛብህ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – በላይ አባይነህ – የአብስራ ሙሉጌታ

ዱላ ሙላቱ – ሮጀር ማላ – መስዑድ መሀመድ – አስናቀ ሞገስ

ምስጋናው መላኩ – ዳዊት ፍቃዱ – መሐመድ ኑርናስር