ዴቪድ በሻህ እና የትውልደ ኢትዮጵያውን ተጫዋቾች ምልመላ ጉዳይ

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች የሆነው ዴቪድ በሻህ በውጭ ሀገር በተለያዩ ሊጎች የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን የመመልመል እና ለብሄራዊ ቡድኑ የመሰለፍ እድል እንዲያገኙ የማድረግ ሃላፊነት ተሰጥቶት ስራ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በቅርብ ቀንም Transfermarket ከተሰኘው ታዋቂ የእግር ኳስ ድረ ገጽ ጋር ስለዚህ ጉዳይ ቆይታ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏ ትልቅ መነቃቃትን እንዳመጣ የተናገረው ዴቪድ የ Transfermarket ድረ ገጽን በመጠቀም የተለያዩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ማግኘት መቻሉን ይናገራል፡፡ “ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ተበታትነው ይገኛሉ፡፡ መጀመሪያ የምናደርገው ከክለቦቻቸው ጋር መወያየት ሲሆን ከዛም በመቀጠል ተጫዋቾችን እና ቤተሰባቸውን ለማናገር እንሞክራለን፡፡ ስራው በተጀመረበት ወቅት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲጫወቱ ማሳመን ከባድ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ተጫዋቾቹን ባናገርኩበት ወቅት ያገኘሁት መልስ ግን በጣም ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡”

ከዚህም በተጨማሪ ዴቪድ ያነሳው ነጥብ ኢትዮጵያ እንደ እግር ኳስ ሀገር አትታይም የሚለው ነው፡፡ የአውሮፓ ክለቦች ሆኑ መልማዮች ተጫዋቾችን ሲፈልጉ አይናቸውን የሚያሳርፉት በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ላቅ ያለ የቴክኒክ ችሎታ ቢኖራቸውም በሀገራቸው የሚያገኙት ደሞዝ ከፍተኛ በመሆኑ እንደ ግብጽ እና ደቡብ አፍሪካ አይነት ጠንካራ ሊጎች ላይ ራሳቸውን እንዲሞክሩ አያስችላቸውም በማለትም ጨምሯል፡፡

ይህንን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሲሰጥ እንደዚህ ብሏል፡ “ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ እምቅ ችሎታ አለ፡፡ ስለዚህ በሚመጡት አመታት የትኩረት ማረፊያ እንደሚሆን ማሰብ እንችላለን፡፡ በውጭ ሀገር የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ማካተት በሜዳ ላይ ከሚኖረው ተጽዕኖ በተጨማሪ እግር ኳሳችን ላይ ብዙ አይኖች እንዲያርፉ ምክንያት ይሆናል፡፡ ተጫዋቾቹ እዚህ ሲመጡ ስላሉበት ክለብ መጠየቃቸው አይቀርም ከዛም በተጨማሪ ብሄራዊ ቡድኑ ውጭ ሀገር ካሉ ክለቦች ጋር ስምምነትን መፍጠር ይቻላል፡፡ “