ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የዊልያም ጎል እና በረከት በመጨረሻ ደቂቃ ያዳናት የፍፁም ቅጣት ምት ኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ቡና በጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ የተጠቀመውን አሰላለፍ ሳይቀይር ሲገባ መከላከያዎች ከባህር ዳሩ ጨዋታ ባደረጓቸው ለውጦች ቢኒያም ላንቃሞ እና ዓለምአንተ ካሳ በአዲሱ አቱላ እና ሰመረ ሀፍተይ ቦታ ተተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሞራል ድጋፍ በማድረግ የተጀመረ ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ይዘው በጀመሩት ጨዋታ እንቅስቃሴው በመከላከያ ሜዳ ላይ ያዘነበለ ሆኗል። በአንፃሩ መከላከያዎች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚን ሲያነፈንፍ ይስተዋል ነበር። ሆኖም የጨዋታው ቀዳሚ ሙከራ 13ኛው ደቂቃ ላይ የታየ ሲሆን ደኃይሌ ገብረትንሳይ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ አቡበከት ናስር በግንባሩ ቢገጭም ክሌመን ቦዬ ሳይቸገር ይዞበታል።


መከላከያዎች በሂደት መነቃቃት የታየባቸው ሲሆን አጋማሹን ተሻግረው ወደ ቡና ሳጥን መቅረብ ከቻሉባቸው አጋጣሚዎች አንድ ከባድ ሙከራ አድርገዋል። 20ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ ከዓለምአነተ ካሳ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።

የጦሩ መነቃቃት ከወሀ ዕረፍቱ በኋላ ጋብ ሲል የቡና ቅብብሎች በሂደት አደገኛነታቸው መታየት ጀምሯል። ዊሊያም ሰለሞን እና አበበከር ናስር ከሳጥን ውስጥ ያደረጓቸው እና ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችም ታይተዋል። ከሁሉም በላይ ግን 34ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የቀኝ መስመር ጥቃት በሮቤል ተክለሚካኤል እና የአብቃል ፈረጃ ጥምረት የፈጠሩት ቡናዎች የአብቃል ወደ ውስጥ ከላከው ኳስ ያልተጠቀሙበት የግብ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር።


የሁለቱ ተጫዋቾች ጥምረት በግራ መስመር ተከላካዩ ዳዊት ማሞ ላይ የቁጥር ብልጫ ወስዶ በቀጣይ የፈጠረው የግብ ዕድል ግን ግብ ሆኗል። 39ኛው ደቂቃ ላይ በዛው ቀኝ መስመር ኃይሌ ፣ የአብቃል እና ሮቤል የፈጠሩትን የአንድ ሁለት ንክኪ ሮቤል መሬት ለመሬት ወደ ግብ ሲልከው ዊሊያም ሰለሞን አምልጦ በመግባት ግብ አድርጎታል።

መከላከያዎች ከግቡ በኋላ መነቃቃት ታይቶባቸዋል። በዚህም 41ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሷል። ቡድኑ 43ኛው ደቂቃ ላይ ሲጠብቀው የቆየው የመልሶ ማጥቃት ዕድል ተከፍቶ ወደ ቡና የመከላከል ወረዳ ሲቀርብ ቢኒያም በላይ ለኦኩቱ ኢማኑኤል ያሳለፈለትን ኳስ ጋናዊው አጥቂ ሞክሮ በአቤል ማሞ ድኖበታል።


ከዕረፍት መልስ በግራ የታየባቸውን ክፍተት ለመድፈን በሚመስል መልከ ቢኒያም ላንቃሞን በብሩክ ሰሙ የተኩት መከላከያዎች በጨዋታ እና በቆሙ ኳሶች መነሻ ጫና በመፍጠር ቡናዎች በረጅሙ ኳስ እንዲያርቁ ማስገደድ ጀምረው ነበር። ሆኖም ያለቀለት የግብ ዕድል ሳያገኙ የአጋማሹ ከባዱ ሙከራ በቡና በኩል የታየ ሲሆን 58ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ከመሀል ሜዳ የጣለትን ኳስ አበበከር በግራው አክርሮ መትቶ ቦዬ ይዞበታል።

ቀሪው የጨዋታ ጊዜም ጦሩ የተሻለ ያጠቃበት እና ቡናዎች የመልሶ ማጥቃት መልክ ይዘው የታዩበት ሆኗል። መከላከያዎች አደገኛ ዕድል ለመፍጠር የተቃረበት ግን 83ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ቢኒያም በላይ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የላከው ኳስ አደገኛ የነበረ ሲሆን ቴዎድሮስ በቀለ ጨርፎ አውጥቶታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ብሩክ ሰሙ በዛው መስመር ተከላካዮችን አታሎ ያሳለፈውን ኳስ ለቢኒያም ቢያደርሰውም ቢኒያም ወደ ግብ የላከውን ኳስ አስራት ቱንጆ ከመስመር ላይ ጎል ከመሆን አድኖታል።

88ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተቀይሮ የገባው ኤርሚያስ ኃይሉ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ለመያዝ ባደረገው ጥረት የመጨረሻ ሰው የነበረው አቤል ማሞ ጥፋት ሰርቶበታል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩም የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥጠው አቤልን በሁለተኛ ቢጫ አስወጥተዋል። አጋጣሚውን ቢኒያም በላይ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ግን በተቀየረው ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ድኗል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና የ1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና ደረጃውን ከ13ኛ ወደ ዘጠነኛ አሳድጓል።