ከፍተኛ ሊግ | ጌዲኦ ዲላ የአሰልጣኝ ለውጥ ሲያደርግ የተጫዋቾች ዝውውርንም ፈፅሟል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ስር የተደለደለው ጌዲኦ ዲላ ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ ከነበረው አሰልጣኙ ጋር በመለያየት እና በምትኩ ረዳቱን በሀላፊነት በመሾም የአዳዲስ ተጫዋቾች ዝውውር አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ተካፋይ ክለብ የሆነው ጌዲኦ ዲላ ለ2014 የሊጉ ውድድር ቀደም ብሎ አሰልጣኝ ደረጀ በላይን መቅጠሩን ገልፆ የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ የጥቅማ ጥቅም ጉዳዮች መግባባት ባለመቻላቸው ከ2011 እስከ 2013 ድረስ ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት እና በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ማገልገል የቻለው ስመኘው ገመዳን በቦታው የቀጠረ ሲሆን ክለቡን ለረጅም ዓመት በአምበልነት የመራውን ሳሙኤል ቦጋለን ረዳት በማድረግ ለውድድር ራሱን እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ቡድኑ ያስፈረመ ሲሆን የነባሮችን ውልም ሲያድስ ወጣት ተጫዋቾችንም አሳድጓል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በጅቡቲ ሊግ በመጫወት ያሳለፈው ግብ ጠባቂው ሀምዲ ቶፊቅ በድጋሚ የቀድሞው ክለቡ ጌዲኦ ዲላን ሲቀላቀል በተመሳሳይ አጥቂው ክንዴ አቡቹም ዳግም የቀድሞው ክለቡን ከቡታጅራ ከተማ መቀላቀል ችሏል። ከዚህ ቀደም በወልድያ የተጫወተው እና አምና በአርባምንጭ ከተማ ቆይታ የነበረው አጥቂው በድሩ ኑር ሁሴን ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን የተገኘው እና በውሰት ከዚህ ቀደም ለደቡብ ፓሊስ መጫወት የቻለው አማካዩ ሉክ ፓውሊኒዮን ጨምሮ ፣ በክሪ መሀመድ (ተከላካይ ከሀላባ ከተማ) ፣ ሰለሞን ብሩ (ተከላካይ ከሀላባ ከተማ) ፣ ዝናው አበበ (ተከላካይ ከኢኮስኮ) ፣ ናትናኤል ሰለሞን (አማካይ ከአርባምንጭ ከተማ) ፣ ኪሩቤል ተካ (አማካይ ከሀላባ ከተማ) ፣ ተስፋዬ በቀለ (አማካይ ከየካ ክፍለከተማ) ፣ አምባዬ ኢሳያስ (አማካይ ከይርጋጨፌ አካባቢ) እና የቀድሞው የቡታጅራ ከተማ እና ባለፈው የውድድር አመት በሀድያ ሆሳዕና ያሳለፈው አጥቂው ድንቅነህ ከበደ የአሰልጣኝ ስመኘው አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡

ክለቡ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ ተካልኝ ሀይሌ (ግብ ጠባቂ) ፣ መልካሙ (ግብ ጠባቂ) ፣ ዘላለም ሽፈራው (ተከላካይ) ፣ መልአሊን ብርሀኑ (አማካይ) ፣ ግርማ ፈይሳ (አማካይ) ፣ ሙሉቀን ተስፋዬ (አማካይ) ፣ ምናሴ ወጋየው (አማካይ) ፣ ቢኒያም በቀለ (አማካይ) ፣ አገኘሁ ብርሀኑ (ተከላካይ) ፣ ዘላለም አበራ (ተከላካይ) እና ይሁን ገላጋይ (ተከላካይ) ውላቸው ሲራዘምላቸው ዳዊት አሰፋ ፣ አቤኔዘር ፣ ሀይሌ አዳነ ፍሬዘር አንለይ ፣ ብሩክ በፀሎት ፣ ውብሸት ሀይሌ እና ምንተስኖት ከበደ የተባሉ ወጣቶችንም ወደ ዋናው ቡድን መቀላቀሉን ሶከር ኢትዮጵያ ክለቡ ከላከላት ዝርዝር መረጃ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል፡፡