ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የሰባተኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ዳሰሳ እንዲህ ቀርቧል።

እስካሁን አንድ ጨዋታ ብቻ ድል ያደረገው አዳማ ከተማ ዳግም ከድል ጋር ለመገናኘት እና ደረጃውን ለማሻሻል በነገው ጨዋታ ታታሮ እንደሚጫወት እሙን ነው።

በደረጃ ሰንጠረዡ አስራ አንደኛ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር ተጫውቶ ነጥብ ሲጋራ መሻሻል የታየበት እንቅስቃሴ አድርጓል። በተለይ ደግሞ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ይዞ ለመጫወት ሲሞክር ታይቷል። እርግጥ ቶሎ ውጤት ከመፈለግ በሚመስል ሁኔታ ግን የኳስ ፍሰቱ ጥድፊያ ይስተዋልበታል። ይህ ደግሞ በተጋጣሚ የመከላከል ሲሶ ላይ ኳሶችን እንዲያመክኑ ያደረጋቸው ይመስላል። ምናልባት ይህ ጥቅፊያ ስክነት በተሞላበት የውሳኔ አሰጣጥ ተገርቶ ተጫዋቾቹ የሚጫወቱ ከሆነ ግን አዎንታዊ ውጤት ሊያገኙ ይችላሉ። በተለይ ደግሞ ፈጣኖቹ አጥቂዎች ከተከላካዮች ጀርባ ለመሮጥ የሚሄዱበት ርቀት ተጋጣሚ ሀሳቡን ትቶ እንዲያጠቃ በር ስለማይከፍት እምብዛም ጫናዎች ሲበረታባቸው አይታይም። ነገ ግን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት እጅግ ቀጥተኛ ሆኖ ሲጫወት የነበረውን ጊዮርጊስ መግጠማቸው ፈተናቸው ጠና እንዲል የሚያረግ ይመስላል።

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቡድኑ ቀድሞ ግብ እያስተናገደ መሆኑ ተጋጣሚን ለማስከፈት ብዙ እንዲለፋ እያደረገው ነው። ከዚህም መነሻነት የጨዋታውን ሁሉንም ደቂቃዎች በእኩል መጠን በከፍተኛ ትኩረት ማከናወን የግድ ይለዋል። ከዚህ ውጪ ግን ቡድኑ በሚፈጥረው ጫና በርካታ የቆሙ ኳሶችን ሲያገኝ ይታያል። ምናልባት አጠቃቀማቸው የተሻለ ከሆነ ደግሞ እንደ አንድ የግብ ምንጭ ሊጠቀሙበት ይችላሉ (ከአዲስ አበባ ጋር ከቅጣት ከሲዳማ ቡና ጋር ደግሞ ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረጉ ኳሶች ማግባታቸው ልብ ይሏል)።

እስካሁን በሊጉ አንድም ሽንፈት ያላስተናገደው ብቸኛው ክለብ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም ይህንን ሪከርድ ለማስቀጠል እና ከሊጉ መሪ ፋሲል ላለመራቅ ነገም ጠንክሮ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።

ሀዋሳ ከተማን ሁለት ለአንድ ሲረቱ የቀደመ ቀጥተኝነታቸውን ያገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነገም በዚሁ አቀራረባቸው አዳማን እንደሚገጥሙ ይታመናል። በተለይ ደግሞ በሁለቱ መስመሮች ላይ ፈጣኖቹን አጥቂዎች ያማከለ አጨዋወት በመከተል ግቦችን ለማግባት ሊጥሩ ይችላሉ። በስድስተኛ ሳምንት ድንቅ ሆኖ ያመሸው አቤል ያለው ደግሞ ታታሪነት በተሞላበት አጨዋወቱ ለተከላካዮች ፈተና ሊቸር እንደሚችል ይታሰባል። ከእርሱ በተጨማሪ ደግሞ አይምሬ የሳጥን ውስጥ አጥቂ መሆኑን ከጨዋታ ጨዋታ እያስመሰከረ የሚገኘው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እስማኤል አውሮ-አጎሮ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ መናገር ይቻላል።

ከወራት በፊት ከቀጠሯቸው ክሮዋት አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ጋር በስምምነት የተለያዩት ጊዮርጊሶች በሀዋሳው ጨዋታ የነበራቸው ተነሳሽነት እና ፍላጎት ነገም እንዲቀጥል ሲጠበቅ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ግን ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርጉት ሽግግር ሲጋለጡ ነበር። አዳማ ከተማ ካሉት ፈጣን አጥቂዎች መነሻነት ደግሞ ይህ ችግር ነገም ከተደገመ ሊቀጣ ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን ከሌሎች ሦስት ክለቦች ጋር በጣምራ የሊጉ ሁለተኛ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደው ክለብ የሆነው ጊዮርጊስ (ከአዳማ እኩል) ከሁለተኛ ሳምንት በኋላ ድል ካላደረገው አዳማ የሚመጣበትን ፈተና ለመመከት ጠጣርነቱ ያስፈልገዋል።

አዳማ ከተማ ነገም የፊት መስመር አጥቂው ዳዋ ሁቴሳን ግልጋሎት አያገኝም። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከነዓን ማርክነህ እና በረከት ወልዴን ከጨዋታው ውጪ አድርጎ ወደ ሜዳ ይገባል።

ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ የሚመሩት ይሆናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም 38 ጊዜያት የተገኛኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀያውን በማሸነፍ የተሻለ ሪከርድ ይዟል። አዳማ ከተማ በአንፃሩ ሰባት ጊዜ ሲረታ አስራ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸውም ጊዮርጊስ 51 አዳማ ከተማ ደግሞ 26 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ሚሊዮን ሰለሞን – አሚኑ ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – አብዲሳ ጀማል – አሜ መሐመድ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም – ሀይደር ሸረፋ

አቤል ያለው – እስማኤል አውሮ-አጎሮ – አማኑኤል ገብረሚካኤል