በሀዋሳ ሲሰጥ የቆየው የካፍ ዲ ላይሰንስ ስልጠና ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና በሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥምረት የተዘጋጀው የካፍ ዲ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠና ለአስራ አንድ ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ከዓመታት መቋረጥ በኋላ ካፍ በአዲስ መልኩ እንዲሰጥ በላከው ኮንቬንሽን መሰረት ሀገራት የአሰልጣኞች የላይሰንስ ስልጠናን መስጠት ከጀመሩ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም የካፍን ትዕዛዝ በመቀበል የካፍ ዲ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠናን በአዲስ አበባ ፣ ባህር ዳር እና አዳማ በመስጠት ጅምሩን ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ለአራተኛ ጊዜ ለአስራ አንድ ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን እና በሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን የጋራ ጥምረት በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ሲሰጥ ሰነባብቶ በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

በካፍ ኢንስትራክተር እና በአሁኑ ሰአት የሰበታ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እየሰሩ በሚገኙት ዳንኤል ገብረማርያም የኮርስ ዳይሬክተርነት የተሰጠው እና ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና እንስቶቹን ኢንስትራክተር ሰላም ዘርአይ እና በኃይሏ ዘለቀን በአሰልጣኝነት ያካተተው ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና በክፍል እና በሜዳ ተግባር ታግዞ ለ60 ሰአታት ለሰላሳ ሰልጣኞች ብቻ የካፍን ህግ በጠበቀ መልኩ ሲሰጥ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን በስልጠናው ተካፋይ የሆኑ አሰልጣኞችም በቀጣይ ወደ ሲ የላይሰንስ ስልጠና ለመሸጋገር በተግባር ወደ ስልጠናው አለም ገብተው ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚገባ የኮርሱ ዳይሬክተር ዳንኤል ገብረማርያም አስረድተዋል፡፡

ስልጠናው በዛሬው ዕለት ሲጠናቀቅ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አሬራ ፣ አቶ ባህሩ ጥላሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዋና ፀሀፊ ፣ አቶ አክሊሉ አለሙ የሲዳማ ክልል ወጣቶች እና ሴቶች ቢሮ የወጣቶች ዘርፍ ምክትል ሀላፊ እንዲሁም አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት እና ኢንስትራክተሮች ሰልጣኞች እና መሰል አካላት በመዝጊያው ዕለት ተገኝተዋል፡፡የሲዳማ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ ለሰልጣኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ለሰልጣኞቹ ጠንከር ያለ የስራ መመሪያ ሀሳብን አጋርተዋል፡፡ በመቀጠል አቶ ፍሬው እንዲሁም አቶ ባህሩ ጥላሁን ንግግር ካደረጉ በኋላ ለሰልጣኞቹ የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን ሰልጣኝ አሰልጣኞችም ለኢንስትራክተሮቹ ያዘጋጁትን ሽልማት በማበርከት ፕሮግራሙ ተደምድሟል፡፡