ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ 

የዘጠነኛው ሳምንት ማሳረጊያ በሆነው ጨዋታ ዙሪያ ቀጣዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በዕኩል 11 ነጥቦች ላይ የሚገኙት ሁለቱ ተጋጣሚዎች እስከ አራተኝነት ከፍ የማለት ዕድልን በሚሰጣቸው ጨዋታ ይገናኛሉ። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በተመሳሳይ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሀዋሳ እና አርባምንጭ ሰሞንኛ ውጤቸው ባሰቡት መንገድ የሄደ አይመስልም። ሁለቱም እስካሁን ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብ ያልቻሉ ሲሆን አርባምንጭ ከተማ አራት ተከታታይ ጨዋታቶችን ነጥብ ተጋርቶ ሀዋሳ ደግሞ ወጣ ገባ የሆኑ ውጤቶችን እያስመዘገበ እዚህ ደርሰዋል። 

ከውጤት ፍላጎታቸው በተጨማሪ ከቡድኖቹ የአጨዋወት ዘይቤ አንፃር ስንመለከተው ጨዋታው ፈጣን ሽግግሮችን ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይችላል። ተጋጣሚዎቻቸው ቅብብሎችን እንዳይጀምሩ ለማድረግ የሚጥሩት አርባምንጮች ነገም ተመሳሳይ ዕቅድ እንዲሚኖራቸው ሲጠበቅ ይህ በራሱ ሀዋሳ ከተማዎችን ወደ ቀጥተኛ አጨዋወት እንዲያመዝኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። በዚህም ከኋላ ወይንም ከጥልቅ የአማካይ ክፍል ወደ ሦስቱ የሀዋሳ ከተማ አጥቂዎች የሚላኩ ኳሶች አደገኝነታቸው ሊታይ የሚችልበት ዕድል አለ። በእርግጥ ከእንቅስቃሴ ባለፈ የሀዋሳ የፊት መስመር ተሰላፊዎች የአጨራረስ ብቃት እንደቡድኑ ውጤት ሁሉ መዋዠቅን እያሳየ መሆኑ ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን አንዱ ድክመት ሆኖ መቀጠሉ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የማጥቃት ሽግግርን መከወን መቻላቸው ብቻውን ውጤታማ ላያደርጋቸው ይችላል።

አርባምንጭ ከተማዎች አሁን ላይ እየተገበሩ የሚታዩት አጨዋወት በራሱ ለተጋጣሚ አስቸጋሪ ቢሆንም ውጤታማነቱን ይበልጥ ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ኳስን አፍነው ለማስጣል እርምጃቸው ከጥፋት የፀዳ ሆኖ ለቀጣዩ የጨዋታ ሂደት የሚያመቻች መሆን ይገባዋል። በነገውም ጨዋታ የሀዋሳን የኋላ ክፍል ለማፈን የሚያደርጉት ጥረት የኳስ ስርጭቱን ከማቋረጥ ባለፈ ስኬታማ በሆነ ሽግግር የግብ ዕድሎችን ወደ መፍጠር ካላደገ መባከኑ የሚቀር አይመስልም። አካላዊ ጉሽሚያዎች ሊበረክቱበት በሚችለው ጨዋታ አርባምንጮች በሜዳው ቁመት የሚኖራቸው የተጨዋቾች ርቀት እንዲሁም ከተከላካይ ጀረባ የሚተዉት ቦታ ከተጋጣሚያቸው ለሚያገኙት ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ምላሽ  መጠን ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ፀጋሰው ድማሙን በቀይ ካርድ መድሀኔ ብርሀኔን ደግሞ በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት አያሰልፍም። አማካዩ አብዱልባሲጥ ከማልም ከጉዳቱ ያላገገመ ሲሆን ፀጋአብ ዮሐንስ ግን ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በመጨረሻ የድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ያነሱት ተከላካያቸው  አሸናፊ ፊዳ ቅጣቱን ጨርሶ ወደ ሜዳ ይመለሳል። ከአሸናፊ በተጨማሪም አብነት ተሾመ ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና ፍቃዱ መኮንን ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ ራምኬል ሎክ ግን አሁንም አይኖርም። 

ጨዋታው በፌደራል ዳኛ አባይነህ ሙላት መሪነት ይከናወናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 14 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከዚህ ውስጥ ስድስቱ ጨታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ አምስት ጊዜ አርባምንጭ ደግሞ ሦስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ ግቦች 16ቱ የሀዋሳ 12ቱ ደግሞ የአርባምንጭ ሆነው ተመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

መሀመድ ሙንታሪ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ዮሐንስ ሱጌቦ

ወንድማገኝ ኃይሉ – ዳዊት ታደሰ – በቃሉ ገነነ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ይስሀቅ ተገኝ 

ወርቅይታደሰ አበበ – በርናንድ ኦቺንግ – አሸናፊ ፊዳ – ሙና በቀለ

ሀቢብ ከማል – እንዳልካቸው መስፍን – አንዱዓለም አስናቀ – መላኩ ኤሊያስ

ፀጋዬ አበራ – ኤሪክ ካፓይቶ