​የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከእረፍት መልስ የሚደረግበት ቦታ ታውቋል

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ በአስረኛ ሳምንት ሲቀጥል በአዳማ ከተማ ይደረጋል ቢባልም ውድድሩ ወደ ሌላ ከተማ መዞሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት በጥሩ ሁኔታ እየተደረገ የሚገኘው የሀገራችን ትልቁ የሊግ እርከን ውድድር ዘጠኝ ሳምንታትን በሀዋሳ ከተማ አከናውኖ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት እና ውድድር ታህሣሥ 15 መቋረጡ ይታወሳል። ቀድሞ በተያዘው መርሐ-ግብር መሰረት ከአፍሪካ ዋንጫው መልስ በአዳማ ከተማ የአምስት ሳምንታት ቆይታን ፕሪምየር ሊጉ እንደሚያደርግ ቢጠበቅም ጨዋታውን ለማስተናገድ የተመረጠው የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተሰጠው ቀነ ገደብ መሠረት ዝግጁ ባለመሆኑ ውድድሩ ወደ ሌላ ከተማ ዞሯል።

ድረ-ገፃችን ከአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሠይፈ ባገኘችው መረጃ መሠረት የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በዋናነት እንዲያስተካክላቸው የተቀመጡትን የፓውዛ እና የመጫወቻ ሜዳ ጉዳይ በሚፈለገው ደረጃ አለማሟላቱን ተከትሎ ውድድሩ ወደ ሌላ ከተማ ዞሯል። በተለይ ደግሞ ውድድሮችን በምሽት ለማከናወን የሚረዳውን ፓውዛ ለመግጠም ጨረታ ቢወጣም ተጫራቹ አካል ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው በመጠየቁ ነገሮች በታሰበላቸው መንገድ እንዳይጓዙ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። ይህንን ተከትሎም ከ10ኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ አጋማሽ ድረስ (15ኛ ሳምንት) ሊጉ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ድሬዳዋ ከተማ እንደሚደረግ ተረጋግጧል።

በትናንትናው ዕለት የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌን ጨምሮ የቦርድ አባላት እንዲሁም የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ አባላት ወደ ስፍራው (ድሬዳዋ) አምርተውም የከተማውን ዝግጁነት እንደቃኙ ተነግሮናል። በቅኝታቸውም ድሬዳዋ ዓምና የነበረውን የመጫወቻ ሜዳ ምቹነት ክፍተት እጅግ በጥሩ ሁኔታ እንደቀረፈ እና አመቺ በሆነ መልኩ ሜዳው እየተስተካከለ እንደሆነ ወደ ስፍራው ካቀናው ልዑክ ሰምተናል። 

አቶ ክፍሌ ጉዳዩን ሲያስረዱን “መጫወቻ ሜዳው እጅግ ተሻሽሏል። እንደውም ትንሽ ቀን ብትሰጡት ከዚህ የተሻለ እናደርገዋለን ብለውናል። ይህ በጣም የሚያስደስት ነው። ከመጫወቻ ሜዳው ውጪም ከነበሩት የአርቴፊሻል እና አሽዋ የመለማመጃ ሜዳዎች ውጪ አዲስ ሙሉ ሳር የተነጠፈበት የመለማመጃ ሜዳም ተዘጋጅቷል።” ብለውናል።

ሊጉን ከ10ኛ ሳምንት ጀምሮ ለማስተናገድ ተራዋ ያልነበረው ድሬዳዋ ዋናው ሜዳውን እና የልምምድ ሜዳዎችን በፍጥነት ከማስተካከል በተጨማሪም እንግዶችን ለማስተናገድ በሆቴል እና ተያያዥ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እየሰራች ያለችው ስራም የሚደነቅ መሆኑን አቶ ክፍሌ አክለው ገልፀውልናል።