በምድብ አንድ የተደለደሉ አራት ሀገራት ወደ ማግሪብ ያመራሉ

ደረጃውን በጠበቀ ስታዲየም እጦት ምክንያት ወደ ሞሮኮ ተጉዘው ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሀገራት ታውቀዋል።

የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚያስተዳድረው ካፍ የመጫወቻ ስታዲየሞችን ጥራት የተመለከተ አዲስ ህግ ካረቀቀ በኋላ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ዝቅተኛው የስቴድየም ጥራት ደረጃ ማሟላት ባለመቻላቸው በሜዳቸው ጨዋታዎቻቸውን ማካሄድ አልቻሉም ፤ ቁጥራቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።

አሁን ደግሞ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚገኝበት ምድብ የተደለደሉት ሴራሊዮን ፣ ጊኒ ቢሳውና ቡርኪናፋሶ በሀገራቸው ካፍ የሚጠይቀውን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጭ የሚያደርጉ ይሆናል። ይህንን ተከትሎም ሦስቱም ሀገራት በተመሳሳይ ሞሮኮ ላይ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን ለማድረግ ከውሳኔ ላይ ደርሰዋል። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ አራቱ የምድቡ ተሳታፊዎች በሞሮኮ ጨዋታዎቻቸው ያከናውናሉ።

የሞሮኮ እግርኳስ ፌደሬሽን ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ከአራቱ ሀገራት በተጨማሪ ዩጋንዳ ፣ ጊኒ ፣ ታንዛንያ፣ ሶማልያ፣ ቻድ ፣ ኒጀር ፣ ማዳጋስካር ፣ ናሚቢያና ዛምቢያ ሞሮኮን ምርጫቸው እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል። ከዚ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን የሚያካሂድበት ስታዲየምም ተለይቷል። ብሔራዊ ቡድኑ ሕዳር 5 ከሴራሊዮን ፤ ሕዳር 11 ደግሞ ከቡርኪናፋሶ ጋር የሚያደረገው ጨዋታ ኤል ጃዲዳ በሚገኘው ኤል አብዲ ስታዲየም እንደሚያከናውን ተረጋግጧል።

ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጋር በተያያዘ ሌላ መረጃ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ከማጣሪያ ውድድሩ ውጭ መሆኑ እየተገለፀ ይገኛል። በማጣርያው ሞሮኮ ፣ ዛምቢያና ሌሎች ሦስት ሀገራት በሚገኙበት ምድብ አምስት የተደለችው ኤርትራ ህዳር 6 ሞሮኮን በመግጠም ከዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ውድድሮች ትመለሳለች ተብሎ ቢጠበቅም የመወዳደሯ ዕድል እንዳከተመለት ለኤርትራ እግር ኳስ ቅርበት ያላቸው ታማኝ ግለ-ሰቦች በመግለፅ ላይ ናቸው።