የኢትዮጵያ ዋንጫ | የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ በሁለት ሜዳዎች በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል።

በጫላ አቤ

በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እና በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውሎ ስድስት ጨዋታዎች ተደርገውበታል።

አዲስ አበባ ከተማ 0-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ረፋድ 4 ሰዓት ላይ በተደረገው የሁለተኛው ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ  በመጀመሪያው አጋማሽ በኤፍሬም ጌታቸው የሚመራው አዲስ አበባ ከተማ በመከላከሉ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያሳዩ ሲሆን በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ጥሩ የሆነ የኳስ ፍሰት እና የተሻለ የኳስ ቁጥጥር አስመልክተውናል። ይህንን ተከትሎም ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ባደረጉት ኤሌክትሪኮች በኩል 22ተኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ካሳሁን ከርቀት ግሩም ኳስ በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ቢያረጉም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የበላይነቱን በመውሰድ በመስመር በኩል ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል ። 72ተኛው ደቂቃ ላይም የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ የሆነው በሽር ደሊል ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ በእጁ ኳስ በመንካቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጫና ውስጥ ሆነው ቢያሳልፉም ምንም ግብ ሳያስተናግዱ ጣፋጭ ድል አሳክተው ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል።

*በተመሳሳይ ሰዓት ሀዋሳ ላይ በተደረገው ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማ በዳዊት ሽፈራው ሁለት ግቦች አዲስ ከተማ ክ/ከተማን 2-0 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

ኮልፌ ክ/ከተማ 2-2 ሞጆ ከተማ

ከምሳ መልስ 8 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ከፍተኛ በሆነ የጥንቃቄ አጨዋወት የኋላ መስመራቸውን በማጠናከር የተጫወቱ ሲሆን በአጋማሹም ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ተደርጎበት ያለ ምንም ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኮልፌ ክ/ከተማ ተሽለው የተገኙበት አጋማሽ ሲሆን በከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው ተጫውተዋል። በአንጻሩ ሞጆ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎም 50ኛው ደቂቃ ላይ ኮልፌ ክ/ከተማ ያገኙትን የግብ ዕድል ዋቸሞ ጳውሎስ ወደ ግብ ቀይሮት ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ጨዋታው በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥሎም 70ኛው ደቂቃ ላይ ሞጆዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ዕድል ፍቃዱ ገሪባ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ሆኖም በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ተቀይሮ የገባው የኮልፌ ክ/ከተማው ተጫዋች ሉካ ፓውል ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ድጋሚ መሪ ማድረግ ሲችል መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ የሞጆ ከተማው ተጫዋች ያሬድ ሽመልስ ባስቆጠራት ግብ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።

አሸናፊውን ለመለየት በተደረገ የመለያ ምት ኮልፌ ከተማዎች 4ለ3 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

*በተመሳሳይ ሰዓት ሀዋሳ ላይ በተደረገው ጨዋታ ደብረብርሃን ከተማ በፍጹም ተስፋማርያም እና በኃይሉ ተሻገር ግቦች ባቱ ከተማን 2-1 በመርታት ወደ ቀጣይ ዙር ተሸጋግሯል። አቤኔዘር ሕዝቅኤልም የባቱን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ተጫዋች ነው።

ጅማ አባ ጅፋር 1-2 ወልዲያ ከተማ

10፡00 ላይ በተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በፊልሞን ገ/ፃዲቅ እና በአናኒያ ጌታቸው የሚመራው ጅማ አባጅፋር ጥሩ የኳስ ፍሰት እና ግሩም ቅብብል ያሳዩ ሲሆን በወልዲያ ከተማ በኩል በነጋ በላይ እና በአለኝታ ማርቆስ በመመራት በጥብቅ የመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። አጋማሹም በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያ ከተማዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የፈጠሩትን የግብ ዕድል አለኝታ ማርቆስ ወደ ግብ በመቀየር ወልዲያ ከተማን መሪ ማድረግ ሲችል ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በጅማ አባጅፋሮች በኩል 55ኛው ደቂቃ ላይ ከፊልሞን ገ/ፃዲቅ የተሻገረለትን ኳስ ከፍያለው ካስትሮ በድንቅ አጨራረስ ግብ አድርጎት ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ የተነቃቁት ጅማ አባጅፋሮች ደጋግመው ግብ ለማስቆጠር የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲጥሩ በአንፃሩ ወልዲያ ከተማዎች የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት በመውሰድ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። 66ኛው ደቂቃ ላይም ወልዲያ ከተማዎች በዚሁ እንቅስቃሴ ያገኙትን የግብ ዕድል ኃይሌ ጌታሁን መረብ ላይ አሳርፎት ቡድኑን በ 2ለ1 ውጤት አሸናፊ ማድረግ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎም ወልዲያ ከተማ ወደ ቀጣይ ዙር ተሸጋግሯል።

*በተመሳሳይ ሰዓት ሀዋሳ ላይ በተደረገው ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ በያሬድ መኮንን ሁለት ግቦች እና በለገሠ ዳዊት አንድ ግብ ወሎ ኮምቦልቻን 3-0 ረትቶ ወደ ቀጣዩ ዙር የተሸጋገረ ሌላኛው ክለብ ሆኗል።