አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የመጀመሪያ ቅድመ ጨዋታ መግለጫቸውን ሰጥተዋል

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በመጪው ሳምንት በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከሴራሊዮን እና ቡርኪናፋሶ አቻቸው ጋር የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች አስመልክቶ ቅድመ ጨዋታ መግለጫቸውን ሰጥተዋል።

አሰልጣኙ በሰጡት ገለፃ በጀመረው መግለጫው አሰልጣኝ ገብረመድህን ቅዳሜ ምሽት ልምምድ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ከተጫዋቾቻቸው ጋር መከተል ስለሚፈልጉት የጨዋታ መንገድ እና ተጫዋቾች ሊከተሏቸው ስለሚገቡ የዲሲፕሊን መመርያዎች ዙርያ ሰፊ ውይይቶችን ስለማድረጋቸው ያነሱ ሲሆን ከስብስቡ የተቀነሱ ተጫዋቾች የግድ የተጫዋቾች ቁጥር መቀነስ ስላለባቸው እንጂ በቀጣይ የስብስቡ አካል እንደሆኑም አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም የትላንቱ የወዳጅነት ጨዋታ ላይ የሚፈልጉትን የጨዋታ መንገድ ከመተግበር አንፃር የመቆራረጥ ነገሮች ቢኖሩም ጥሩ ተስፋን መመልከታቸውን የተናገሩ ሲሆን በቀጣይነት በሚኖሯቸው ቀሪ አራት ልምምዶች ቀሪ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

በማስከትልም በስፍራው ከነበሩ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምለሽ የተሰጠባቸው ሲሆን ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል

ሊተገብሩ ከሚፈልጉት የጨዋታ መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጫዋቾቻቸው ላይ ከማስረፅ አንፃር

“በራሳችን ሜዳ ብዙ የመቆየት ነገር አይኖርም ፤ ከዛ አንፃር ባለፉት ልምምዶች ላይ የተወሰኑ ለውጦችን ተመልክቻለሁ ግን አሁን ቢሆን ልጆቹ ክትትል ይፈልጋሉ። በወጥነት ለመተግበር መቸገሮች ቢኖሩም ተጫዋቾቹ ለመቀበል ያላቸው ፍላጎት ጥሩ ነው። በልምምዶች ወቅት በዋናነት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው አንደኛው በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ ለመቆየት ዝግጁ መሆን ሁለተኛው ደግሞ ከፍ ባለ ጫና መጫወት አስፈላጊ ስለሚሆን ለዚያ የሚያስፈልጉንን ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት ነው። እንደተባለው ጊዜው አጭር እንደመሆኑ እና ከተለያየ የጨዋታ መንገድ ውስጥ የመጡ ተጫዋቾች በመሆናቸው ነገሩ አስቸጋሪ ቢሆንም ለተጫዋቾች መንገዳችንን በግልፅ ካስቀመጥንላቸው ለመተግበር ይጥራሉ። ከዚህ አንፃር ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። ይህን ሁሌ እንዲከተሉ ለማድረግ ጥረት እና ጊዜ ይፈልጋል አንዳንዴ ኳሱን ይጀምሩና ወደ እኛ መንገድ ለመምጣት የኔን ትዕዛዝ የመጠበቅ ነገር አለ ነገር ግን ሲሄዱ ደግሞ በጣም ጥሩ ነው።”

“ሌላው ደግሞ ከኳስ ውጭ ያለን እንቅስቃሴ በጣም ደካማ ነው ፤ ይሄንንም ለማሻሻል በጣም እየሰራን ነው። ሁሌም ቢሆን ኳስ ስናጣ ሁላችንም መሮጥ ይኖርብናል ከዚህ አንፃር መጠነኛ ለውጦች ቢኖርም ይበልጥ በጊዜ ሂደት ግፊት አሳድረን የምንሰራበት ከሆነ ሊመጣ ይችላል።”

ሰለአለልኝ አዘነ መቀነስ

“በስብስቡ በቅድሚያ የተካተቱት ተጫዋቾች በሙሉ በግሌ ተመልክቻቸዋለሁ። ሁሉም ተጫዋቾች የምናወዳድረው በየመጫወቻ ቦታቸው አሁን በስብስቡ ውስጥ ካሉ ልጆች ጋር ነው ለምሳሌ የአለልኝን ማንሳት ካለብን አለልኝ የሚወዳደረው ከናትናኤል እና ጋቶች ጋር ብቻ ነው። በወቅታዊ ብቃት ስንመዝናቸው ግን በተለየ ከእኛ እሳቤ አንፃር በተለይ ከኳስ ውጭ ያለው ነገር ከሁለቱ በጥቂቱ ደከም ያለ በመሆኑ ሳንይዘው ቀርተናል። ነገር ግን አለልኝ ትልቅ አቅም ያለው ወጣት ልጅ ነው በቀጣይም ብሔራዊ ቡድን በሚገባ ማገዝ የሚችል ተጫዋች ነው።”

በከፍተኛ ጫና ለመጫወት የሚያስችል አቅም በተጫዋቾቹ ላይ ካለ

“አቅም መፍጠር ያስፈልጋል ፤ ከዚህ በፊት በሊጉ አንዳንድ ቡድኖች ይህን አጨዋወት ይሞክሩ ይሆናል ነገርግን በወጥነት ሲተገበር አይታይም። ነገር ግን ዕምነቱ ካለ እና በወጥነት መስራት ከቻልክ ልጆቹ ላይ መፍጠር ይቻላል። በከፍተኛ ጫና ለመጫወት ተጫዋቾቹ ካላቸው ዕውቀት እና አቅም ባሻገር አካላዊ ዝግጁነታቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል እኛም በነበረን አጭር ጊዜ በሰራናቸው ቴስቶች በዚህ ረገድ ብዙ ክፍተት አላየንም ዋነኛው ችግር ያለው አዕምሯቸው ላይ ነው። አንዳንዶቹ ኳስ ስናጣ ቆም ብለው በጥቂቱ ተራምደው ሌሎች ባስጣሉት ኳስ ወደ እንቅስቃሴ የመግባት ነገር አለ። ግን እንደ ቡድን ስትሰራ ኳሱ የተበላሸበት ብቻ ሳይሆን በኳሱ አካባቢ ያሉት ሁሉ በጋራ መከላከል መጀመር እንዳለብን ያውቃሉ ነገርግን ለምሳሌ ሱራፌል አጨዋወቱ ይታወቃል። ኳስ ስናጣ የመጀመሪያ ጫና የሚያሳድረው ሰው ግን እሱ ነው። ሌሎችም እንደ እሱ ኳሱን ብቻ ይፈልጉ የነበሩ ልጆች አሉ ግን ወደ እኛ ወደምንፈልገው መንገድ እየገቡ ነው። ተጫዋቾቻችን ላይ የሚታየውን ስንፍና ወደ ታታሪነት ለማምጣት ተደጋጋሚ ሥራ ይፈልጋል ተጫዋቾች የሚከተሉት መሪያቸውን ነው ስለዚህ ከሰጠናቸው ወደምንፈልገው ነገር ማምጣት እንችላለን።”

ስለ አሰልጣኝ ቡድኑ አባላት መሳሳት

“ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው ብሔራዊ ቡድኑ ሰፊ ስታፍ ነው የነበረው። ነገር ግን እኛ ከመጣን በጣም አጭር ጊዜ ነው ነገር ግን ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኝ ፣ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ፣ የቪዲዮ ተንታኝ እና ሌሎች ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉን አምናለሁ። ነገርግን በነበረን አጭር ጊዜ ሁሉንም ነገር ለማሟላት ከባድ ስለነበረ ሥራውን ለማስጀመር በሚያስችል መልኩ አደራጅተን ወደ ሥራ ገብተናል ለጊዜው ከእኛ ጋር የሚሄዱ አካላት ስለሚኖሩም ከእነሱ ጋር ተባብረን የምንሰራ ይሆናል።”

ስለቡድኑ የአጥቂ መስመር አማራጮች

“አሁን ላይ በተጨባጭ ባለው ሁኔታ ትክክለኛ የፊት አጥቂ ማግኘት ከባድ ነው ፤ ትላንት በመጀመሪያው አጋማሽ ከነዓንን እንደተጠቀምነው ላንቀጥል እንችላለን በቀጣይ በሚኖሩን ሥራዎች የሚወሰን ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ተጫዋቾችን የአጨዋወት መንገዱ በራሱ አንጥሮ ይለያቸዋል ትላንትም ሀብታሙን በሁለተኛው አጋማሽ ካስገባን በኋላ በተለየ ጫና ፈጥሮ ከመጫወት አንፃር የተሻለ ነገሮችን አሳይቶናል ስለዚህ ለሁለቱ ጨዋታዎች ከምንፈልገው ነገር አንፃር ይሆናል ያልነውን ሰው የምንጠቀም ይሆናል።” የሚሉት በጥያቄ እና መልስ ወቅትየተነሱ ዓበይት ሀሳቦች ሲሆን በዚሁ መግለጫውም ፍፃሜውን አግኝቷል።