ዮሐንስ ሳህሌ ከሀድያ ሆሳዕና አሰልጣኝነት ራሳቸውን አገለሉ

የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ከክለቡ ተለያይተዋል። ክለቡም ከነገ ጀምሮ በረዳቶቹ እየተመራ ወደ ልምምድ ይመለሳል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2016 የውድድር ዘመን ተሳትፎውን እያደረገ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ የአምስት ሳምንት ጨዋታዎችን በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመራ አድርጎ በሦስት የአቻ ውጤቶች እና በሁለት ሽንፈቶች በሦስት ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ላይ ተቀምጦ ወደ ዕረፍት ማምራቱ ይታወሳል። ከነገ ጀምሮ በአዳማ ከተማ በመሰባሰብ ወደ ዝግጅት የሚገባው ክለቡ በዛሬው ዕለት በክረምቱ ከቀጠራቸው አሰልጣኝ ጋር መለያየቱ እውን ሆኗል።

ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዳስታወቀው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በዛሬው ዕለት ለክለቡ የመልቀቂያ ደብዳቤን ያስገቡ ሲሆን “በቤተሰብ ችግር ምክንያት ሥራዬን መስራት ስላልቻልኩ በክለቡ አሰልጣኝነት መቀጠል አልችልም” ስለማለታቸው እና በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቀዋል።

ከነገ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ዋንጫ እንዲሁም ደግሞ ለፕሪምየር ሊጉ ውድድር አዳማ ላይ ወደ ዝግጅት የሚመለሰው ክለቡ በረዳት አሰልጣኞቹ ዶ/ር እያሱ መርሀፅድቅ እና ግርማ ታደሰ መሪነት ልምምዱን እንደሚያከናውንም ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።