ከፍተኛ ሊግ | የአንደኛ ሣምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ሣምንት ዛሬ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ ፣ ቦዲቲ ፣ ኤሌክትሪክ እና ኦሜድላ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

በአዲስአበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው የጅማ አባ ቡና እና የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አባ ቡናዎች ከራሳቸው የግብ ክልል በተደራጀ የኳስ ቅብብል ለመውጣት ሲሞክሩ አዲስ አበባዎች በአንጻሩ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ በመግባት ተጭነው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም 11ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል አለሰ ከቀኙ የሳጥኑ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ከመሬት ትንሽ ከፍ ብሎ ያገኘው ቢኒያም ታከለ በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎት አዲስ አበባ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ እየወሰዱ የመጡት ጅማ አባ ቡናዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ትዕግሥት በተሞላበት የተረጋጋ የማጥቃት ሂደት ሲቀጥሉ 37ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን ሙከራቸውን አድርገዋል። እስጢፋኖስ ተማም ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ነብዩ ዳንኤል ሲመልስበት አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥም ኩሴ ሞቸራ በጥሩ ክህሎት ለራሱ ባመቻቸው ኳስ ተጨማሪ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ነብዩ አግዶበታል።

ከዕረፍት መልስ አዲስ አበባዎች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ለመጫወት ሲመርጡ ጅማዎች በአንጻሩ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ በመግባት በተለይም በቀኙ የማጥቃት መስመራቸው ከእስጢፋኖስ ተማም በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ 71ኛው ደቂቃ ላይም ራሱ እስጢፋኖስ ተማም በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ በተረጋጋ እና ግሩም በሆነ አጨራረስ አስቆጥሮት ጅማ አባ ቡናዎችን ወደ አቻ መልሷል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው መነቃቃት የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች 93ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው አዲስዓለም ዘውዱ ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከሳጥን አጠገብ የመታው ኳስ በተከላካይ ተጨርፎ መረቡ ላይ አርፏል። በዚህም ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሀዋሳ ሰው ሠራሽ ሜዳ ከቀትር መልስ ቦዲቲ ከተማን ከደብረብርሃን ከተማ ያገናኘው መርሐግብር ቀዳሚው ሆኗል። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ አመርቂ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ሁለቱም ቡድኖች ያላሳዩን ቢሆንም ቦዲቲ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ የተሻለ ቅርፅን ይዘው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ በብዙ መልኩ ከደብረብርሃን በተሻለ በመንቀሳቀስ ወደ ጎል መድረስ የጀመሩት ቦዲቲዎች 56ኛ ደቂቃ ላይ ቀዳሚ ጎላቸውን አግኝተዋል። ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ ዘሩባቤል ፈለቀ ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን መሪ አድርጓል። በበርካታ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾችን የተዋቀረው ደብረብርሃን ከተማ በድጋሚ የኋላ ክፍሉ በሚሰራው መዘናጋት ተጨማሪ ጎል አስተናግዷል። 62ኛ ደቂቃ ላይ የመስመር አጥቂው ክብሩ በለጠ ከሳጥኑ ጠርዝ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ በመጨረሻም ጨዋታው በቦዲቲ ከተማ የ2ለ0 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።



የ 10፡00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ የሣምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሀላባ ከተማን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቷል። ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ኤሌክትሪኮች ከራሳቸው የግብ ክልል ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ ዝግ ያለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ሀላባዎች በአንጻሩ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል። በዚህ እንቅስቃሴያቸውም በርበሬዎቹ 10ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ቴዎድሮስ ወልዴ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ፎሳ ሴዴቦ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ሲመለስ ያገኘው ልደቱ ለማም ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ይህም በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች አጨዋወታቸውን ቀይረው ገብተዋል። በዚህም ሀላባዎች ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ሰጥተው ሲቀርቡ ኤሌክትሪኮች በአንጻሩ በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ከራሳቸው የግብ ክልል ፈጥነው በመውጣት የተጋጣሚያቸውን የግብ ሳጥን በተደጋጋሚ መፈተን ችለዋል። ኤሌክትሪኮች 73ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ሰለሞን ከቅጣት ምት ካደረገው ጥሩ ሙከራ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በጋሻው ክንዴ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ሚኪያስ ካሳሁን በጥሩ አጨራረስ ግብ አድርጎታል። ሆኖም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ሀላባዎች 81ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል በወሰዱት ኳስ ወርቃማ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ቀዝቃዛ የነበረው ጨዋታ በመጨረሻም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ሰው ሠራሽ ሜዳ ላይ የሣምንቱ ማሳረጊያ የሆነው የባቱ ከተማ እና ኦሜድላ ጨዋታ በአሰልጣኝ ወርቁ ደርገባ እየተመራ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገው ኦሜድላ አሸናፊነት ተቋጭቷል። ወጥ ባልሆኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን በቀጠለው በዚህ ጨዋታ ከዕረፍት መልስ 61ኛው ደቂቃ ከቀኝ ወደ ውስጥ የተሻማን ኳስ የባቱ ከተማ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ ተከላካዩ ተመስገን ሽብሩ በራሱ ግብ ላይ ኳሷን አሳርፏት ጨዋታው በኦሜድላ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።