ሲዳማ ቡና ከአሰልጣኙ ጋር ተለያይቷል

የሲዳማ ቡና የቦርድ አመራሮች አሰልጣኙን ጠርተው ከተነጋገሩ በኋላ በስምምነት ለመለያየት ተስማምተዋል።

ከወቅታዊ ውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ መገኘት በሚገባቸው የዝግጅት ጊዜ ተገኝተው ሪፖርት አለመቅረባቸውን ተከትሎ ክለቡ አሰልጣኙ እና ምክትሉ ላይ የዕግድ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በሰዓቱ ያለመገኘታቸው ምክንያት በቤተሰብ የግል ጉዳይ መሆኑን እና የክለቡ አመራራር ይህን አውቆ ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመልሳቸው በደብዳቤ ጠይቀው ነበር። ከትናንት በስቲያ በዚህ ጉዳይ ስብሰባ የተቀመጠው የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ በቀጠይ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በክለቡ በአሰልጣኝነት መቆየት አልያም አለመቆየት ዙርያ የመጨረሻ ውሳኔ ከመወሰኑ አስቀድሞ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን ጠርቶ ለማነገር አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር።

በዚህም መሠረት ትናንት ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር ዘለግ ላለ ሰዓት ሰፊ ውይይት ያደረገው የክለቡ የቦርድ አመራር ከአሰልጣኙ ጋር በስምምነት ለመለያየት መስማማታቸውን ሰምተናል። ከዚህ በተጨማሪም ምክትል አሰልጣኙ ቾንቤ ገብረህይወትም ሲሰናበት በጊዜያዊነት በዕግድ ላይ የነበሩት ሌላኛው ምክትል አሰልጣኝ አረጋዊ ወንድሙ እና ቴክኒካል ዳይሬክተሩ ዓለምባንተ ማሞ ቡድኑን የሚመሩት ይሆናል።