ከፍተኛ ሊግ | የአንደኛ ሣምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬም በሁለቱ ሜዳዎች በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል ነገሌ አርሲ የዕለቱ ብቸኛ ባለ ድል ሆኗል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ ላይ የዕለቱ የመጀመሪያ መርሐግብር ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ እና ስልጤ ወራቤን ሲያገናኝ በመጀመሪያው አጋማሽ በዛ ባለ የግብ ሙከራ ያልታጀበ ነገር ግን ዕረፍት የለሽ የሆነ እንቅስቃሴ ተደርጎበታል። በአጋማሹ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ቀጥተኛ ኳሶችን በመጠቀም በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ስልጤ ወራቤዎች በአንጻሩ ኳስን ከራሳቸው ሳጥን በመመስረት እና መስመሮችን በመጠቀም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ የኦሮሚያ ፖሊሱ ዳንኤል ዳርጌ ከሳጥን አጠገብ አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ የመለሰበት ኳስም በአጋማሹ የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ከነበረው ግለት በመጠኑ ቢቀዛቀዝም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ተሻሽሎ ሲቀጥል በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተጠናክረው በመቅረብ 55ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ዳንኤል ዳርጌ በግሩም ሩጫ ወደ ሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ኃይሌ ዘመድኩን በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ስልጤ ወራቤዎች መልስ ለመስጠት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ ይህ ጥረታቸውም 66ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶላቸዋል። አካሉ አበራ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ያሻገረው እና ሲያምረኝ ዳንኤል በግንባሩ የገጨው ኳስ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ግብ ሆኗል። ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ 82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የስልጤው ስዩም ደስታ በተከላካይ ስህተት ባገኘው ኳስ የሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አሸናፊ አበበ መልሶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ይህም የጨዋታው የተሻለ የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

በሀዋሳ ሰው ሠራሽ ሜዳ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ነገሌ አርሲ እና ወሎ ኮምቦልቻ ተገናኝተውበታል። ከፍ ባለ ተነሳሽነት የጨዋታው ፊሽካ ከተሰማ ጀምሮ ለመጫወት ሲጥሩ የተስተዋሉት ነገሌ አርሲዎች ጎል ማስቆጠር የጀመሩት ገና 6ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ምስጋና ሀገንሳ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ አሊ ቡኖ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በፍጥነት የተጋጣሚ ሜዳ ላይ በመገኘት በመስመር እና በመሐል ለመሐል የቅብብል ኳሶች ፋታ የለሽ የማጥቃት መንገድን የሚከተሉት ነገሌዎች ከደቂቃዎች ቆይታ መልስ ሁለተኛ ጎላቸውን አክለዋል።

ምስጋና ሀገንሳ የኮምቦልቻ ተከላካዮችን የአቋቋም ስህተት ተመልክቶ የሰጠውን በጥሩ አጨራረስ ሠለሞን ገመቹ ከመረብ ጋር አዋህዷት የአሰልጣኝ በሽር አብደላን ቡድን ወደ 2ለ0 መሪነት አሸጋግሯል። ኳስን ከራሳቸው የሜዳ ክልል አልያም በረጅሙ በማሻገር ወደ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል በድግግሞሽ ወሎ ኮምቦልቻዎች መድረስ ቢችሉም በቀላሉ ያገኟቸውን ዕድሎች መጠቀም አለመቻላቸው በተቃራኒው ተጨማሪ ጎል እንዲያስተናግዱም ሆኗል። 31ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ተስፋዬ ከቀኝ ወደ መሐል ይዞ የገባውን ኳስ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ሠለሞን ደምሴ መረብ ላይ አሳርፏት አጋማሹ በነገሌ አርሲ 3ለ0 መሪነት ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ለተመጣጣኝነት የቀረቡ እንቅስቃሴዎች በርክተው ያየን ቢመስልም አሁንም ከጎል ጋር ለመገናኘት ጥረት በማድረጉ ረገድ ነገሌ አርሲ ሻል ያለውን ቦታ ይወስዳል። ወሎ ኮምቦልቻዎች ወደ ጨዋታ ለመግባት ኳስን በማንሸራሸር ከርቀት በሚደረጉ ጠንካራ ምቶች ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቢስተዋልም የስልነት ችግሮቻቸው በመኖራቸው ግቦችን ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በይበልጥ ወደ ጥንቃቄ አድልተው ነገር ግን በመልሶ ማጥቃት አስደንጋጭ ሙከራዎችን ነገሌዎች ሲያደርጉ ብንመለከትም አጋማሹ ግቦችን ሳያስመለክተን በመጨረሻም በነገሌ አርሲ 3ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል።

የ 10፡00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ በዕለቱ ሁለተኛ እና የመጨረሻ መርሐግብር ይርጋጨፌ ቡና  እና ሞጆ ከተማ ተገናኝተዋል። መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚቆራረጡ ኳሶች የሚበዙበት እና የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። ሆኖም 28ኛው ደቂቃ ላይ ግን ይርጋጨፌዎች የተሻለውን የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። መልአሊን ብርሃኑ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ ለግብ ጠባቂው ፈታኝ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ቶማስ ዘገዬ በጥሩ ንቃት አቋርጦበታል። ይህም በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተጫዋቾች መካከል በሚከሰቱ ንክኪዎች በዳኛ ፊሽካ በተደጋጋሚ የሚቆም የነበረ ሲሆን የጨዋታው ግለት እጅግ የተቀዛቀዘ ነበር። ሆኖም ጨዋታው አልፎ አልፎ በሁለቱም በተለይም በሞጆዎች በኩል ጥሩ የኳስ ቁጥጥር ሲደረግበት በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎችም በመጠኑ ተሻሽሎ ቀጥሏል። 81ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው የተሻለው ንጹህ የግብ ዕድል በሞጆዎች ሲፈጠር በግራ መስመር ከቅጣት ምት የተነሳውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው ፍቃዱ ባርባ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበት ያገኘውን ወርቃማ ዕድል ሲያባክነው በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ሌላኛው የቡድን አጋሩ ብሩክ ግርማ ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከረጅም ርቀት በአስደናቂ ሁኔታ በግራ እግሩ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ አካሉ በግሩም ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። በመጨረሻ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ሞጆዎች 88ኛው ደቂቃ ላይም አሸናፊ የሚሆኑበትን ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ የገባው አቤኔዘር ታደሰ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ሀዋሳ ሠው ሠራሽ ሜዳ ላይ አርባምንጭ ከተማን ከሸገር ከተማ በመቀጠል ያገናኘው ጨዋታ በተመሳሳይ ሰዓት ተጀምሯል። የአርባምንጭ ከተማ ፈጣን የሆኑ የሽግግር ኳሶች በአንፃሩ የሸገር ከተማ የተደራጁ የቅብብል መንገዶችን ባስተዋልንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎችን ያህል አርባምንጭ ከተማ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻለበትን መንገድ ተመልክተናል። በአሸናፊ ተገኝ ቀዳሚ የሚሆኑበትን አጋጣሚ አግኝተው ወንድወሰን አሸናፊ በጥሩ ቅልጥፍና ካወጣበት ከደቂቃዎች በኋላ አዞዎቹ ቀዳሚ ጎላቸውን አግኝተዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት አሸናፊ ተገኝ ሲያሻማ በክረምቱ ከንግድ ባንክ ክለቡን የተቀላቀለው ፀጋ አለማየሁ በግንባር ገጭቶ ጎል አድርጓታል። ሸገሮች ምላሽ ለመስጠት በሚመስል እንቅስቃሴ በሳዲቅ ሴቾ አማካኝነት የሚያስቆጭ ዕድልን ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

አስደናቂ ፉክክርን በይበልጥ ያስተዋልንበት ሁለተኛው አጋማሽ ሸገር ከተማ በአላዛር ሽመልስ ተሻጋሪ ኳሶች እንዲሁም በቅያሪ ተጫዋቾች ታግዘው ወደ ጨዋታ በይበልጥ  ራሳቸውን በማስገባት በአርባምንጭ ከተማ ላይ ጫናን ሲያሳድሩ ታይቷል። አርባምንጮች ተጨማሪ ጎልን አስቆጥሮ ለመውጣት ከእንዳልካቸው መስፍን እየተነሱ መሐል ለመሐል በሚሾልኩ እና ፍቃዱ መኮንን የትኩረት ማዕከል ባደረጉ እንቅሰቃሴዎች ቢጫወቱም 87ኛው ደቂቃ ላይ በተከላካዮች ትኩረት ማጣት ግብ አስተናግደዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው ወጣቱ መሐመድ ኑረዲን ሦስት ተጫዋቾችን በድንቅ ሁኔታ አልፎ ለፋሲል አስማማው ሲያቀብለው አጥቂው ነፃ ቦታ ለነበረው ሀይከን ድዋሙ ሰጥቶት ተጫዋቹም ኳሷን ከመረብ አገናኝቷት ጨዋታው በመጨረሻም በ1ለ1 የአቻ ውጤት ተቋጭቷል።