የጣና ሞገዶቹ መብራቱ ሀብቱን ለተጨማሪ ኃላፊነት ሾመዋል

የባህር ዳር ከተማ ቴክኒካል ዳይሬክተር የነበረው ጁኒየር ኢንስትራክተር መብራቱ ሀብቱ የክለቡ ምክትል አሰልጣኝ እና ቪድዮ አናሊሲስ ባለሙያ ሆኖ እንዲሠራ ተመድቧል።

ወጣቱ የጣና ሞገዶቹ ባለሙያ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪውን በእግርኳስ አሰልጣኝነት የሠራ ሲሆን ወደ ጀርመን በመጓዝ በኢንተርናሽናል የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ዲፕሎማውን መያዙ ይታወቃል። በተጨማሪም እዛው ጀርመን UEFA ‘A’ LICENSE  EQUIVALENCE እንዲሁም የ CAF ‘B’ ላይሰንሱን ጭምር የያዘው መብራቱ ሀብቱ በቪድዮ አናሊስስ ሰርተፊኬት አለው።

በጣና ሞገዶቹ  ውስጥ በሠራባቸው ዓመታትም ከቴክኒካል ዳይሬክተርነቱ ጋር ለክለቡ የቪድዮ አናሊስስ ባለሙያ በመሆን የሠራ ሲሆን ታዳጊዎች ላይ ለክለቡ የአስር ዓመት ስትራቴጂካዊ እቅድ በማውጣት ‘የሞገዱ ተስፋ’ በሚል ቃል ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በታዳጊዎች ላይ ትልቅ ፕሮጀክት እንዲሠራ ትልቁን አሻራም አስቀምጧል።

ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እንዲሁም ከአሰልጣኝ ደግአረገ ጋር መሥራት የቻለው ባለሙያው በብሔራዊ ሊጉ ዳሞት ከነማን የመሳሰሉ ክለቦችን በዋና አሰልጣኝነት መምራቱ የሚታወስ ሲሆን በባህርዳር ከተማም የክለቡ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ከደረጄ መንግስቱ ጋር አብረው የሚሠሩ ይሆናል።