​የአሠልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 0-1 ወላይታ ድቻ 

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በጦና ንቦቹ አንድ ለምንም አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች ለሱፐር ስፖርት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

በሁለቱ አጋማሽ ስላደረጉት እንቅስቃሴ?

አንደኛው ዙር ሊጠናቀቅ ሦስት ጨዋታዎች ናቸው የሚቀሩት። እኛ ደግሞ አቅደን የተነሳነው በሁለተኛው ዙር ቡድናችን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ ነው። በሁለተኛው ዙር ሥራ እንዳይበዛብን እዚህ ድሬዳዋ ላይ ነገሮችን አቅልለን ለመሄድ ነው ያሰብነው። በድሬዳዋ ቆይታችን በሦስት ጨዋታ አራት ጎል አግብተን አንድ ጎል ብቻ ነው የገባብን። የገባብንም በራሳችን ስህተት ነው። ዞሮ ዞሮ ታክቲካሊ ዲሲፕሊን የመሆን ጉዳይ ነው። ተጋጣሚያችን ጠንክሮ እንደሚመጣ እናውቃለን። በሁለተኛው አጋማሽም ነቅሎ እንደሚመጣም እናውቃለን። እኔም የነበሩ ክፍተቶችን ለማጠናከር ሞክሬያለው። ይህ ውድድር ነው። ይህንን ውድድር ደግሞ የምንቆጣጠርበት መንገድ ይለያል። ተጋጣሚዎች የእኛን ጎል ለማግኘት ይቸገራሉ። በቀላሉ ጎላችንን አያገኙትም። እንዳልኩት ግን ጣጣችንን በአንደኛ ዙር እንጨርሳለን የሚል ግምት ነው ያለኝ። ምክንያቱም በተጫዋች ዝውውር እና በአንዳንድ ነገሮች ክለቡ ላይ የቤት ሥራ ለማብዛት አልፈልግም። ዞሮ ዞሮ ተጫዋቾቼ ውጤቱን ለማግኘት ሜዳ ላይ ያደረጉት ነገር ቀላል አይደለም። 

ዋንጫ ለማግኘት ዕቅድ አላችሁ?

ውድድሩ ነው ወሳኝ። መጀመሪያ ስታቅድ የቡድኑን በራስ መተማመን ታሳድጋለህ። እኔ ደግሞ ለቡድኑ አዲስ ነኝ። ቡድኑን እንደ አዲስ እያዋቀርኩ ነው ያለሁት። በእያንዳንዱ ጨዋታ እኛ ማድረግ የሚገቡንን ነገሮች ማድረግ ነው የሚገባን። ሁሉንም ጨዋታዎች እንደ ጥሎ ማለፍ ነው የምናየው። ከዚህም በኋላ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችም ከውጤት ጋር እንዲያያዝ እናደርጋለን። አሁን የቀረብን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችንን ማስተካከል ብቻ ነው። ውጤቱን በተመለከተ በእኛ ብቻ የሚወሰን አይደለም በተጋጣሚ ቡድኖች ጥንካሬ እና ድክመት ላይ ይታያል። እኛ ግን መጀመሪያ ላይ ቡድናችን በራስ መተማመኑን ካዳበረ ከዚህ የተሻለ የሚያመጣበት እና የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የማያደርግበት ምክንያት አይኖርም። እያንዳንዱ ነገር ላይ የምናገኛቸው ነጥቦች ወሳኝነት አላቸው። ምንም ይሁን ምንም ግን ድሬዳዋ ላይ የሆነ ነገር ሰርተን መሄድ አለብን ብለን ነው ያቀድነው። ከሞላ ጎደል ከሦስት ጨዋታ ሦስቱን አሸንፈናል። በቀሪ ጨዋታዎች ደግሞ ጠንክረን በድክመቶቻችን ላይ ሰርተን ማረም የሚገባንን አርመን መዘጋጀት ነው።

ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ

ወጣት ተጫዋቾችን መጠቀማቸው ጉዳት ፈጥሮባቸዋል?

ይሄንን ማለት አልችልም። ነገር ግን የተጋጠምነው ቡድን በብልጠት እና ያላቸውን አስጠብቆ በመውጣት በልጠውናል። ከዚህ ውጪ በሌላ ነገር አልበለጡንም። የእኛዎቹ ወጣት በመሆናቸው የተበለጡት ነገር የለም። ግን የባላጋራ ቡድን ያገኛትን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት የሰራው ስራ የተሻለ በመሆኑ እኛ እንዳናገባ አድርጎናል። ወደ ጎልም ብንሄድ ጥሩ ተከላክለዋል። ጥሩ ጊዜ ገለው ተጫውተዋል። በዚህ ነው እንጂ የበለጡን የእኛ ተጫዋቾች ወጣት መሆናቸው የበደለን ብዙ ነገር የለም። የቀረብን ነገርም የለም።

ስለነበራቸው የግብ ማግባት እንቅስቃሴ?

በመጀመሪያው ሆነ በሁለተኛው አጋማሽ ለተጫዋቾቻችን የነገርነው ነገር አንድ አይነው ነው። አንዳንዴ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ሲገቡ የሚያዩትን ነገር አይተው ራሳቸው የሚወስኑት ውሳኔ አለ። ያንን ለመወሰን ነፃ ናቸው። ከዚህ ውጪ ግን ከእረፍት በፊት እና በኋላ ያልነው ነገር የለም። ግን ከእረፍት በኋላ መግፋት የፈለግነው እየተመራን ስለነበረ ነው። ከእረፍት በፊት ደግሞ ገና እረፍት አለ የሚል ነገር ተጫዋቾቹ ስለነበራቸው ሙሉ ለሙሉ ከፍተን ራሳችንን አናጋልጥም የሚል ነው። በኋላ ግን ጨዋታው እየገፋ በሄደ ቁጥር ከኋላ 2 እና 3 ሰው በማቆም ወደ ፊት ለመሄድ ሞክረናል።