​ወልቂጤ ከተማ ባገዳቸው አሠልጣኞች ቅሬታ ቀረበበት 

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወልቂጤ ከተማ የእግድ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው አሰልጣኞች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታ ማስገባታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ከሰሞኑ ከተሰሙ ጉዳዮች መካከል ወልቂጤ ከተማ ከአሰልጣኞቹ ጋር የገባው እሰጣ ገባ ተጠቃሽ ነው፡፡ በ12ኛው ሳምንት ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 4ለ0 ወልቂጤ ከመረታቱ አስቅድሞ እንዲሁም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በክለቡ ተሰራብኝ ያሉትን ጉዳይ በመጥቀስ ከቡድኑ ጋር ሊለያዩ እንደሚችሉ ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፃቸው የሚታወስ ሲሆን ክለቡም ከጨዋታው ማግስት ዋና አሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸውን እና ረዳት አሰልጣኙ እዮብ ማለን ቀሪ የስድስት ወራት ውል እያላቸው በማገድ ተመስገን ዳናን በቦታው መተካቱ ይታወቃል።

ከክለቡ ጋር ከሀምሌ 1 2013 እስከ ሰኔ 30 2014 ድረስ ህጋዊ ውል እያለኝ ከተስማማነው ውጪ ያለ አግባብ ታግጃለው ውሌም በህገ ወጥ መልኩ ፈርሷል እንዲሁም ያልተከፈለኝ ከጥር ወር ጀምሮ ደሞዝ ስላለኝ እንዲከፈለኝ እና እስከ ውሉ ማብቂያ ቀሪ ደሞዜ ይከፈለኝ በማለት እንዲሁም ረዳት አሰልጣኙ እዮብ ማለ ከነሀሴ 1 2013 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ድረስ ውል እንዳላቸው ጠቅሰው ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ውሉ ማብቂያ ድረስ ደሞዜ ይከፈለኝ በማለት በተጫዋቾች ህጋዊ ወኪል እና በህግ ጠበቃው ብርሀኑ በጋሻው አማካኝነት በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ የቅሬታ ደብዳቤያቸውን ማስገባታቸውን አውቀናል።