የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-1 አርባምንጭ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በአርባምንጭ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ተከታዮቹ ሀሳቦች በቡድኖቹ አሰልጣኞች ተሰንዝረዋል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው

“ጨዋታው እነሱ እኛ ሜዳ ላይ መጥተው ተጭነው ነበር የሚጫወቱት። ያንን በምን መልኩ አልፈን እንወጣለን የሚለው ነገር ነበር። በተገቢው የምንሰራበት አጋጣሚ ነበር። እንደገና ሂደቶቹ የሚቋረጡበት ሁኔታም ነበር። እና እንደዛ ዓይነት መልክ ነበረው።

የዛሬው የቡድኑ አቋም ከእስካሁኖቹ ደካማው ስለመሆኑ

” ደካማ ነው ማለት አይቻልም ለእኔ። ከግብ ሙከራ አንፃር ትክክል ነው። እንደዚህ ዓይነት ነገር ከዚህ በፊት በ2012 ከወልቂጤ ጋር ስንጫወት ገጥሞናል ፤ እኛ ሜዳ ላይ በጣም አጥብበው ስለነበር በመጀመሪያው አጋማሽ። ያ ጫና ዘጠና ደቂቃ እንደማይቀጥል እናውቃለን ግን የተጫዋቾቹን በራስ መተማመን ለመጨመር ነው ፤ ኃላፊነቱን ወስደው እንዲጫወቱ። ምክንያቱም ስህተት በሰሩ ቁጥር በራስ መተማመናቸው እየወረደ እንዳይመጣ የማድረግ ስራ ነበር። ኳሶች ቶሎ ቶሎ በተበላሹ ቁጥር ትንሽ ከእንቅስቃሴ የመራቅ በስነ ልቦና የመውረድ ነገር ነበር። ያ ትንሽ ከባድ አድርጎታል።

ቡድኑ በሚፈለግበት የጥራት ደረጃ ላይ ስለሚደርስበት ጊዜ

“እሱን እንግዲህ ተናግሪያለሁ። አንዳንድ ጊዜ ወደ ተጋጣሚ ግብ የምትሄድበት መንገድ ትክክለኛ መሆን አለበት። መሄድ ይቻላል ዝም ብሎ ፤ በረጅም ኳሶች መሄድ ይቻላል። እዛ ደረሼ ትክክለኛ ሙከራ ልሞክርበት እችላለሁ የምንለውን አካሄድ መሄድ አለብን። ከዛ ጋር እየታገልን ነው ፤ ያለው ነገር ጥሩ ነው። ለእኔ ጥሩ ነው። ከውጤት እና ከአንዳንድ ነገር ስታየው ግን የራሳችንን ነገር ለማስቀጠል ባለ ፈተና ውስጥ ነው እየተጫወትን ያለነው። ያው ተገማች የመሆኑ ጉዳይ የሚቀጥል ነው። አንድ የራስህ ነገር እስካለህ ድረስ ተገማች መሆንህ አይቀርም።”

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለጨዋታ ዕቅዳቸው

“የእኛ ቡድን ወጥ የሆነ ጠንካራ አፈፃፀም አለው። ምናልባት ከዚህ በላይ እያደገ የሚመጣ ነገር አለው። በመጀመሪያው አጋማሽ ይበልጥ ተጭነን ነው የተጫወትነው የጎል አጋጣሚ እንዳይፈጠር። ሁለተኛው አጋማሽ ላይም ተመሳሳይ ነው። ግብ ጠባቂው ኳስ ይዞ የመውጣት ጥረት ነበረው። የቁጥር ብልጫ እንዳይኖር ጥረት አድርገናል። ጎሉም ውጤቱም የተሻለ ነገር ነው ብዬ ነው የምወስደው። ትልቁ ነገር ማሸነፋችን ነው።

የግብ ዕድሎችን ስላለመጠቀማቸው

“አሁን ወደ ማሸነፉ መጥተናል። በተወሰነ መልኩ ረጅም ጊዜ ሆኖናል ፤ ጎሎችን ሳናስቆጥር። በእርግጥ ከአንድ ጨዋታ በፊት አንድ አግብተናል። ዛሬ ጎል ማስቆጠራችን ለአጥቂዎችም ለቡድኑም በራስ መተማመን ነው የሚሆነው። በቀጣይ ደግሞ ከአንድ በላይ እንዲሁም ተደጋጋሚ ጎሎችን ማስቆጠር እንጀምራለን።”